ሐምሌ 27, 2026
የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ተከበረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16/2018 (ከመልሚ)የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ባለፉት 75 ዓመታት የተጓዘበትን ታሪካዊ የመንገድ ልማት አሻራዎች በማስታወስ፣ የተቋሙን ስኬቶች በመዘከር እና ለነገው አዲስ የልማት ምዕራፍ ቃል ኪዳን በመግባት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከብሯል።
በዝግጅቱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የቀድሞ የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች፣ የልማት አጋር ተቋማት፣ የሥራ ተቋራጮች፣ አማካሪዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የመስሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ተገኝተዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እንደገለጹት፤ ይህ የ75ኛው ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል ተቋሙ ባለፉት ሰባት አሥርተ ዓመታት ያከናወናቸውን ታላላቅ ሥራዎች የሚዘክርበት ብቻ ሳይሆን ወደፊት የሚጠብቁትን ሀገራዊ ግቦች ለማሳካትም አዲስ ቃል የሚገባበት ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም ተቋሙ በምስረታው ወቅት ከነበረው ውስን አቅም ተነስቶ ዛሬ የሀገሪቱን ገጽታ የሚቀይሩና ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ታላላቅ የመንገድ ፕሮጀክቶችን የማከናወን ብቃት ላይ መድረሱ የሚያኮራ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የመንገድ መሠረተ ልማት ለኢንዱስትሪ ዕድገት፣ ለግብርና ምርታማነትና ለቱሪዝም መስፋፋት ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል በመሆኑ የተቋሙ የወደፊት ጉዞ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በዲጂታል አሠራር የታገዘ እንዲሆን የሚደረጉ የሪፎርም ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ በበኩላቸው፣ በዓሉ ተቋሙ ባለፉት 75 ዓመታት ከአንደኛው የሀገሪቱ ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ ሕዝቦችን በማገናኘት ያከናወናቸውን ሥራዎች የሚያደንቅበት ብቻ ሳይሆን፣ ሀገራዊ ራዕይን ዕውን ለማድረግና የተጀመሩ የልማት ምዕራፎችን ለማጠናከር አዲስ ጉልበት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር መሐመድ አብዱራሕማን የኢመአ የ75 ዓመታት ጉዞ ባለፉት ዓመታት ብዛት ብቻ የሚለካ ሳይሆን በራዕይ፣ በቁርጠኝነት፣ በሙያዊ ብቃትና በትውልዶች ትጋት የተገነባ ታሪክ መሆኑን ገልጸዋል።
በተቋሙ ምስረታ ወቅት የነበረው የሀገሪቱ የመንገድ አውታር 6, ሺህ 400 ኪሎ ሜትር ብቻ እንደነበር ጠቅሰው፣ ዛሬ ግን 182 ሺህ 232 ኪሎ ሜትር የደረሰ ሰፊ የመንገድ አውታር መገንባቱን ጠቁመዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ቀድሞ ከነበሩት የአውራ ጎዳና ፕሮግራሞች ተነስቶ እስከ መንገድ ሴክተር፣ እንዲሁም ከ1989 ዓ.ም ወዲህ በተተገበሩ ተከታታይ የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራሞች አማካኝነት የተከናወኑ የመንገድ ግንባታና ጥገና፣ የድልድይ ልማት፣ የመንገድ ንብረት አስተዳደር፣ የመንገድ ደኅንነትና የተቋማዊ አቅም ግንባታ ላይ ከፍተኛ እመርታ ተመዝግቧል።
በቀጣይም ተቋሙ በጥራት፣ በዘላቂነት፣ በደኅንነት፣ በአካባቢ ጥበቃና በዘመናዊ የንብረት አስተዳደር መርሆዎች ላይ በመመሥረት የመንገድ ልማቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ለሦስት ቀናት በሚቆየው በዚህ የበዓል መርሃ-ግብር ፣ የተቋሙን የ75 ዓመታት የመንገድ ልማት ጉዞ የሚያሳዩ የፎቶና የሰነድ ኤግዚቢሽኖች፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማሳያዎች እንዲሁም የውይይት መድረኮች ይከናወናሉ።
ከዚህም በተጨማሪ የእውቅና አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓቶችና የባሕል ዝግጅቶችን ጨምሮ የተለያዩ ይዘት ያላቸው ፕሮግራሞች የዚሁ ሁነት አካል ናቸው።