ጥቅምት 13, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28 ቀን 2019 (ከመልሚ):- የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደርን ላለፉት 4 ዓመታት በዋና ዳይሬክተርነት የመሩት ኢንጅነር መሐመድ አብዱራሕማን ከመስከረም 28፣ 2019 ጀምሮ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የከተማ እና መሠረተ-ልማት ሚንስትር ሆነው ተሹመዋል።

ኢንጅነር መሃመድ አብዱራህማን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ  በሲቪል ምህንድስና ሙያ፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከእንግሊዝ ሀገር በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት የሙያ ዘርፍ አግኝተዋል።

ኢንጅነር መሀመድ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የአገራችንን የመንገድ ዘርፍ በማሻሻልና የስርጭት አድማሱን በማስፋፋት ረገድ ከ20 አመታት በላይ በምህንድስና ባለሙያነት ፣ የሪጅን ዳይሬክተርነት፣ በምክትል ዋና ዳይሬክተርነት ደረጃ ባሉ ኃላፊነቶች የጎላ ድርሻ አበርክተዋል።

እንጂ. መሀመድ የኢትዮጵያ ዲዛይን ፣ ሱፐርቪዥን እና ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝንም በዋና ዳይሬክተርነት ፣  ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርን በዋና ዳይሬክተርነት በብቃት መርተዋል።

ኢንጅነር መሀመድ አብዱራህማን ባለፉት 24 ዓመታት  በመንገድ ዘርፍ  ከባለሙያነት እስከ ከፍተኛ የስራ ሃላፊነት በሚያገለግሉበት ወቅት ፤ በአገር ውስጥና በውጭ  አገር በዘርፋ ላይ የሚያተኩሩ የተለያዩ  ስልጠናዎችን ወስደዋል። ያገኟቸውን ዕውቀቶች መሰረት በማድረግም ከመንገድ ዘርፉ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ጥናቶችን በማካሄድ እና ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀት ለዘርፉ ስኬት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ቤተሰብ ኢንጅነር መሐመድ አብዱራሕማን “እንኳን ደህና መጡ “ እያለ፣ መልካም የስኬት እና የውጤታማነት ዘመን እንዲሆን ከልብ ይመኛል!

Posted in: ዜና