ህዳር 25, 2026

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15/2019 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ክቡር መሀመድ አብዱራህማን (ኢ/ር) ከዘጠኝ ኩባንያዎች የተውጣጡ የጃፓን የልዑካን ቡድን ዓባላትን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

የልዑካን ቡድን ዓባላቱ፣ የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ስላለው ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለማወቅና የቅድመ-ኢንቨስትመንት ጉብኝት ለማድረግ የመጡ መሆናቸውን ገልጸው በተሰማሩባቸው ዘርፎች፡- በመንገድ መሠረተ-ልማት፣ በአረንጓዴ ልማት፤ በታዳሽ ኃይል፣ በቆሻሻ አያያዝና አወጋገድና ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል እንዲሁም ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በሀገራችን ስላለው ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ማወቅና ሀገሪቱ የቀረጸቻቸውን የልማት ስትራቴጂዎች በቅርበት ማወቅ የጉብኝታቸው ዓላማ መሆኑን የገለጹት የልዑካን ቡድኑ ዓባላት በሀገሪቱ ስላለው የልማት እንቅስቃሴና የወደፊት ዕቅድ በሚመለከት ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ጋር ለመወያየት አቅደው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚሁ መሠረት ለልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ስላለው ምቹ የንግድና የኢንቨስትመንት ሁኔታ እና የመንግስት የወደፊት ዕቅድን በተመለከተ በዋና አማካሪ በአቶ ተስፋዬ ወ/ሚካኤል ዝርዝር መረጃ አቅርበው ልዑካኑ ስለኩባንያዎቻቸው ዝርዝር መረጃ በመስጠት ላቀረቧቸው ጥያቄዎች በሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በመጨረሻም ክቡር ሚኒስትሩ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት በሀገራችን እየተሰሩ ባሉ ስራዎች የተገኙ ለውጦች ምን እንደሚመስሉና የመንግስት የወደፊት አቅጣጫ ምን እንደሆነ፣ በቀጣይ ለመስራት ስለተቀረጹ የልማት ስትራቴጂዎች በዝርዝር በማንሳት የጃፓን ኩባንያዎች በሀገራችን የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ በሠፊው ቢሰማሩ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚረዳ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተለይም ጃፓን በቴክኖሎጂ ሠፊ ልምድና ተሞክሮ ያላት ሀገር በመሆኗ ለሀገራችን ዕድገት ጠቃሚ አጋር መሆኗን በማስታወስ ኩባንያዎች ወደ ሀገራችን መጥተው በተሰማሩባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች ቢሰማሩ ፍላጎታቸው መሆኑንና ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጸውላቸዋል፡፡ 

የልዑካን ቡድኑ ዓባላትም ስለተደረገላቸው አቀባበልና በውይይት ለተነሱ ጥያቄዎች የተብራራ መረጃ ስለተሰጫቸው አመስግነው በጉብኝታቸው እና ባደረጉት ውይይት መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

Posted in: ዜና