ጥቅምት 10, 2025

አዲስ አበባ፣መስከረም 9/2018 ዓ.ም (ከመልሚ)

የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር፣ የመሠረተ-ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ፣ ክቡር አቶ የትምጌታ አስራት በኮሪያ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ፣ በኮሪያ ኮንትራክተር ከጎሬ ማሻ ቴፒ ድረስ እየተገነባ ያለውን የ120 ኪሎ ሜትር የመንገድ ስራ ፕሮጀክት የግንባታ ሂደት በተመለከተ ኮንትራክተሩ በስራ ሂደት የገጠመውን ችግር ለመፍታት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ለመምከር በኮሪያ አምባሳደር የተመራውን የልዑካን ቡድን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በኮሪያውያኑ በኩል የክፍያ መዘግየትና ለመንገድ የተቀየሱ ቦታዎችን ሙሉ በሙሉ ከዕዳ ነጻ ከማድረግ አንጻር ውስንነቶች መኖራቸውንና ይህም ፕሮጀክቱን በተገባው ውል መሠረት አጠናቆ ለማስረከብ ችግር እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡

በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር በኩል በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ባለቤትነት በመንገድ መሠረተ-ልማት ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች በርካታ የመሆናቸውን ያህል እነዚህ ፕሮጀክቶች የያዟቸውን ስራዎች በተገባው ውል መሠረት እንዲያጠናቅቁ ለማድረግ በስራ ሂደት የሚገጥሟቸውን ችግሮች ተከታትሎ መፍታት የመንግስት ቁርጠኛ አቋም መሆኑን ክቡር አቶ የትምጌታ አስራት ገልጸውላቸዋል፡፡

የኮሪያ አምባሳደርና ልዑካቸውም የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት እንደዚህ ባለ መንገድ ተቀራርቦ ለመነጋገርና የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መቻሉን አድንቀው ለተደረገላቸው አቀባበል በማመስገን ፍሬያማ ውይይት በማድረጋቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

Posted in: ዜና