ታህሳስ 22, 2025
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3/2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ፣ ክቡር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት የኮሪያ የቢዝነስ ቡድን ዓባላትን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡
የልዑካን ቡድኑ ዓባላት የኢትዮጵያ ጉብኝት በኮንስትራክሽንና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ለመስራትና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ እንደሆነ በኮሪያውያኑ የተገለጸ ሲሆን ኩባንያቸው (ኮስካ) በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ ለማጥናት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ ተነግሯል፡፡
ክቡር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያን መርጠው በመምጣታቸው መደሰታቸውን ገልጸው አሁን ላይ ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ የምትገኝ ሀገር መሆኗን በመግለጽ ለሚኒስቴር መ/ቤቱ የተሰጠውን ተልዕኮ አብራርተው ለሚኒስቴር መ/ቤቱ ተጠሪ የሆኑ ሦስት ተቋማት መኖራቸውንና ተግባርና ኃላፊነታቸው ምን እንደሆነ ገልጸውላቸዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በማያያዝ በኢትዮጵያ በርካታ በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ያሉ መሆናቸውን በመግለጽ በኢትዮጵያ በመሠረተ-ልማት ዘርፍ ያለው ፍላጎት ሰፊ በመሆኑ የኮሪያ ኩባንያዎች በኮንስትራክሽን፣ በቴክኖሎጂ እና በአቅም ግንባታ ዘርፍ ያላቸውን አቅም ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት አብረው ቢሰሩ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ በመግለጽ ኮሪያውያኑ ከኢትዮጵያ ጋር አብረው ለመስራት ላሳዩት ፍላጎት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላትም ለተደረገላቸው አቀባበልና ለተሰጣቸው ገለጻ አመስግነዋል፡፡