ጥቅምት 27, 2025
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11/2018፣ (ከመልሚ)
ተጠሪነታቸው ለከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የመሠረተ-ልማት ዘርፍ የሆኑ ተቋማት የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የእቅድ አፈጻጸም የተጠሪ ተቋማቱ የስራ ኃላፊዎችና የማኔጅመንት አካላት በተገኙበት ተገምግሟል፡፡
የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ያቀረቡት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር፣ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን መ/ቤቶች ናቸው።
በሁሉም ረገድ ጥሩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆናቸው በሪፖርታቸው ተመላክቷል፡፡ በተሰሩ ስራዎች የተገኙ ውጤቶች የተሻሉ መሆኑ ቢነገርም የሰው ኃይል እጥረት ለስራቸው እንቅፋት እንደሆነባቸው ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡
በቀረቡት የሪፖርት ሠነዶች መነሻነት ውይይት ተደርጓል ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከተቋማቱ አመራሮች ዝርዝር መረጃዎችና ተጨማሪ ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል፡፡
የመሠረተ-ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ የትምጌታ አስራት በተነሱ ጥያቄዎችና በተሰጡ ምላሾች ዙሪያ ተጨማሪ አስተያየት ሰጥተዋል ። በማጠቃለያቸውም በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር እና በተዋረድ ባለው መዋቅር ለመተግበር ታቅዶ በዝግጅት ምእራፍ ላይ ለሚገኘው ሀገራዊ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም እና ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ ትኩረት በመስጠት የኢንዱስትሪውን ማነቆ በዘላቂነት መፍታት የሚቻልበት ዕድል እንዳለ አንስተው ለዘርፉ ችግሮች ሁነኛ መፍትሄ የሚያመጡ በመሆናቸው በትኩረት ሊሰራባቸው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን ዘርፋችን ከፍተኛ ሀገራዊ ኃላፊነትን ያለበት በመሆኑ ፈጠራና ፍጥነትን፣ ትጋትና ጥራትን ማዕከል በማድረግ ተቀናጅቶና ተናብቦ በጋራ በመስራት የዘርፉን ዕቅድ ለማሳካት እንዲያስችል በሚኒስቴር መ/ቤቱ እንደ ዘርፍ የተዘጋጀውን የጋራ ስምምነት የዕቅድ ሠነድ የተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች ከዘርፉ ሚኒስትር ዴእታ ጋር ተፈራርመዋል፡