ጥቅምት 10, 2025

በፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አማካኝነት የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ ስልጠና ለከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር አመራርና ባለሙያዎች  ተሰጠ፡፡  በስልጠናው ላይም ከዋናው መ/ቤት የተውጣጡ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም  የዐብይ፣ የቴክኒክና የንዑሳን ኮሚቴ ዓባላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በትናንትናው ዕለት የተጀመረውን የስልጠና መድረክ በይፋ ያስጀመሩት በሚኒስቴር መ/ቤቱ የሥራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ  አቶ አበራ አመንታ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደ ሀገር ትልቅ አጀንዳ ሆኖ እየተሰራበት ያለው ትልቅ የለውጥ እርምጃ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም እንደሆነ ገልጸዋል።

ቀደም ሲል የነበሩ የሪፎርም ስራዎች ነጻና ገለልተኛ ያልነበሩ፤ ብዝሀነትና አካታችነትን ማዕከል ያላደረጉ፤ የምዘና ስርዓቱም ቀልጣፋና ውጤታማ ያልነበረ፤ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጡ ለይስሙላ ያህል እንጂ ተጨባጭ ለውጥ ያላመጣ እና ከውጤት ይልቅ ሂደት ላይ የተኮረ በመሆኑ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጡ ከእርካታ ይልቅ የተገልጋይ ምሬትን የፈጠረ ስለሆነ አሰራርን ማዕከል ያደረገ የመንግስት አስተዳደርና  አገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርም ወቅቱ በሚጠይቀው አግባብ በአዲስ መልክ ማዘጋጀት ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡

ስልጠናውን የሰጡት የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የትራንስፎርሜሽንና የለውጥ ስራ አመራር መሪ ስራ አስፈጻሚው ወርቁ ደጄኔ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሲቪል ሰርቪስ መሪነት በሁሉም የመንግስት ተቋማት በሦስት ዙር (በዝግጅት ምዕራፍ፣ በትግበራ ምዕራፍ እና በማጽናትና የፈጠራ ደረጃ ላይ ለመድረስ በሚቻልባቸው ስራዎች ዙሪያ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት) በሚሰሩ የሪፎርም ስራዎች ላይ የሚያጠነጥነውን ስልጠና በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት ቀደም ሲል የነበረው የሲቪል ሰርቪስ አሰራር የነበሩበትን ጉድለቶች በመዳሰስ በሪፎርም ጥናቱ መለየቱን አስረድተዋል፡፡

ሪፎርሙ ያስፈለገበትን ገፊ ምክንያቶች፤ የሪፎርሙን ዋና ዋና አምዶች መለየትን እና ከሪፎርሙ አምዶች አንጻር መከናወን ያለባቸው ዋና ዋና ተግባራት ምን ምን እንደሆኑ እንዲሁም የሪፎርሙን ዕቅድ ማዘጋጀትና መገምገምን በተመለከተ ያሉ ጉዳዮችን በዝርዝር አብራርተዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ተገኝተው የስራ መመሪያ የሠጡት የሪፎርም አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢው የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዳኤታ ክቡር አቶ የትምጌታ አስራት  ባስተላለፉት መልዕክት ሀገራችን ኢትዮጵያ ከአስተሳሰብና ከአሰራር ጋር በተገናኘ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት እየተጋች ያለች ሀገር መሆኗን በመግለጽ ሪፎርሙ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ጠንካራና ብቁ የሆነ ተቋም ለመፍጠር በዘርፋችን የሚታዩ በርካታ ጉድለቶችን ማረም እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

እጅግ በጣም በፍጥነት እየተለወጠች ባለች ሀገር ውስጥ የምንኖር እንደመሆናችን መጠን የለውጡ አባል ብቻ ሳንሆን መሪም ለመሆን ሀገርን መቀየር የእኛ ኃላፊነት ስለሆነ በቂ የሰው ኃይል፣ ፍላጎትና አቅም ስላለን ወደንና ፈቅደን በከፍተኛ ትኩረት፣ ፍላጎትና ተነሳሽነት ወደ ሁሉም አቅጣጫ የሚናበብና የሚያሰራ አተገባበር እንዲኖረን በትጋት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ለዚህም ሦስት መሰረታዊ ጉዳዮችን ከዚህ የስልጠና መድረክ መውሰድ እንደሚያስፈልግና እነሱም ፡- ሪፎርም የምናደርገው ለምንድን ነው፤ ምኑንስ ነው ሪፎርም የምናደርገው፤ እንዴትስ ነው ሪፎርም የምናደርገው ለሚሉት ጉዳዮች አንድ ዓይነት መረዳት ይዞ መውጣት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

በስልጠና መርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይም በዘርፉ በስምንት ቡድኖች በተደራጁ ኮሚቴዎች የዘርፉን የትኩረት መስኮች መሠረት በማድረግ ሊሰሩ የታቀዱ ተግባራትን ዝርዝር በፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ከተዘጋጀው ፍኖተ-ካርታ ጋር በማነጻጸር በጋራ መገምገም ተችሏል፡፡

Posted in: ዜና