መጋቢት 19, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8/2018 ዓ.ም (ከመልሚ) የሲዳማ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ በከተማና መሠረተ-ልማት ዘርፍ በዝግጅት ምዕራፍ እየተሰሩ ባሉ የሪፎርም ስራዎች ዙሪያ ጥናቱን በክልል ደረጃ ለመጀመር የሚያስችል የልምድ ልውውጥ አካሄደ፡፡

የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር በሁለተኛ ዙር ወደ ስራ ለመግባት ከተመረጡ የፌዴራል ተቋማት መካከል አንዱ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት የዝግጅት ምዕራፍ ጥናቱን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ይህ በሦስት ምዕራፍ ተከፍሎ በፌዴራል ተቋማት የሚተገበረው የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም በተያዘለት ዕቅድ መሠረት እንዲከናወን ለማድረግ ሚኒስቴር መ/ቤቱና ተጠሪ ተቋማቱ ተቀናጅተው እያጠኑት ያለው ጥናት በተዋረድ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ማዕከል ድረስ ደረጃውን ጠብቆ የሚወርድና አደረጃጀቱም ወጥነት ኖሮት ከላይ አስከታች መዋቅሩን ጠብቆ የሚተገበር በመሆኑ የሲዳማ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ጥናቱን ከወዲሁ ለመጀመር የሚያስችለውን የልምድ ልውውጥ ለማግኘት ከእናት መ/ቤቱ የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የዝግጅት ምዕራፍ ጥናቱን በተመለከተ በዛሬው ዕለት የልምድ ልውውጥ አድርጓል፡፡

በተደረገው የልምድ ልውውጥም ወደ ቅድመ-ዝግጅት ጥናት ለመግባት የሚያስችላቸውን ግንዛቤ እንዲያገኙ በሪፎርም ጥናቱ የዐብይ ኮሚቴ አባልና ጸሐፊ በሆኑት የተቋማዊ ለውጥ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አዱኛ ዓለሙ እና በጥናት ቡድን ሰብሳቢዎች አማካኝነት ገለጻና ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን ከሲዳማ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ የመጡ የስራ ኃላፊዎች ላነሷቸው ጥያቄዎችና ሌሎች የጥናት ሂደቱን የተመለከቱ ጉዳዮች ዝርዝር መረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ቡድኑም በተደረገው ገለጻና ማብራሪያ ከተጠበቀው በላይ የተፈለገውን መረጃ ማግኘት መቻሉንና በክልሉ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት እየሰራ መሆኑን በመግለጽ ተጨማሪ ለውጥ ለማምጣትም ሪፎርሙ አስፈላጊ መሆኑን በማመን ቀድሞ ወደ ጥናት ለመግባት የተነሳሳ በመሆኑ ለተሰጠው ገለጻና ማብራሪያ ምስጋናውን በማቅረብ ወደ ፊትም ሪፎርሙ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ድጋፍና እገዛ እንደማይለየው በመግለጽ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

Posted in: ዜና