ታህሳስ 12, 2025
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23/2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)
የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር አመራርና ሠራተኞች የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት መከበር ሕገ መንግሥታዊ ዋስትናን ያረጋገጠውን የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት የጸደቀበትንና ለ20ኛ ጊዜ “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን በዓል በዛሬው ዕለት በሚኒስቴር መ/ቤቱ አዳራሽ በጋራ አክብረዋል፡፡
መድረኩን በክብር እንግድነት ተገኝተው በንግግር የከፈቱት የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ካሊድ አብዱራህማን በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በዴሞክራሲ እና በፌዴራል ሥርዓት ግንባታ ያሉትን ተስፋዎችና የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች እንዲሁም በሀገራዊ ሪፎርሙ፣ በተሰሩ የልማት ስራዎች እና በመሰል ተግባራት የተጓዝንባቸውን ርቀቶች በማስታወስ የእርቀ ሠላም ኮሚሽን በሀገራችን ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የጀመራቸውን ጥረቶች ከዳር ለማድረስ የሁሉንም ዜጋ ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም ብዝሃነት ባለበት ሀገር ውስጥ ሆነን የማህበረሰብ መዋቅሮቻችንን አጠንክረን በመያዝና ጤናማ የፌዴራል ሥርዓትን በማጎልበት ተደምረን የጋራ ራዕያችንን በሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ ስለሚገባን ለሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት የራሳችንን የዜግነት ድርሻ ልንወጣ ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስትር ዴኤታ፣ ክብርት ወ/ሮ ሄለን ደበበ በተመሳሳይ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ሥር እንዲሰድና እንዲዳብር ለማድረግ ለሥርዓቶቹ መገንባት ተፈላጊ የሆኑ አስተሳሰቦችን መላበስ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ለውይይት የተዘጋጀው ሠነድ በክብርት ሚኒስትር አማካሪ አቶ በየነ መለሰ በዝርዝር የቀረበ ሲሆን በመጨረሻም ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ሀሳብና አስተያየቶች ከመድረክ ምላሽ በመስጠት መርሃ-ግብሩ ተጠናቋል፡፡