ጥቅምት 27, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2018 ዓ.ም (ከመልሚ) የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የማኔጅሜንት አባላት የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን በጠንካራ ጎን እና በክፍተት የተስተዋሉ ጉዳዮችን በጥልቀት ገምግመዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ የተቋሙ አመራሮች በተሳተፉበት ያለፉትን ሦስት ወራት አፈጻጸሞች በስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ በዝርዝር ሪፓርት ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በሪፓርቱ መሠረት ሰፊ ውይይት የተደረገባቸው ጉዳዮች የመኖሪያ ቤት ግንባታና ተደራሽነት፣ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ፣ ከተማን ሚመለከቱ ፖሊሲዎችና የህግ ማዕቀፎች፣ የከተሞች የአረንጓዴ አሻራና የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ፣ ከተሞች ምግብ ዋስትናና ሴፍቲኔት፣ ከመሬትና ሪል ፕሮፐርቲ እንዲሁም አጠቃላይ ስለአገልግሎት አሰጣጣችን ለውስጥም ሆነ ለውጭ ተገልጋይ ደንበኞች ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ  በዝርዝር ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ መንግሰት ለከተሞች በሰጠው ልዩ ትኩረት ባለፉት ሦስት ወራት መላው የተቋሙ አመራር እና ሰራተኛው ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብና የሥራ ተነሳሽነት በከተሞች ከፍተኛ የሆነ ዕድገት እየተመዘገበ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

ዘመኑ የማንሰራራት ዘመን ነው ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ የታሪክ አሻራዎች ብርሃን እየፈነጠቁ የዜጎች ተስፋ ከጊዜ ወደጊዜ እየለመለመ መምጣት የታየበት ወቅት መሆኑን ጠቅሰው በተለይ የህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ፣ የከተሞች የኮሪደር ልማት፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ኢኒሸቲቮች፣ በመንግሰትና በግሉ ዘርፍ የሚከናወኑ የቤት ልማቶች፣ ሚኒስቴር መስሪ ቤቱ ለከተሞች በሚያደርገው ድጋፍና ክትትል ከተሞች በገቢ ሪፎርም ራሳቸውን ለመቻል ገቢያቸውን አሟጠው ለመጠቀም እየሄዱበት ያለው ጉዞ ሊበረታታ ይገባል ብለዋል፡፡

የምንተገብረው ሪፎርም የሀገራችንን ከተሞች አስከታችኛው መዋቅር የሚስተዋሉ ዘርፈ-ብዙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና ብልሹ አሠራሮች ተወግደው መንግስትና ህብረተሰቡን ከማራራቅ ይልቅ ሊያቀራርቡ የሚችሉ አካሄዶች በሁሉም ከተሞች እውን እንዲሆኑ የሚታቀዱ ዕቀዶችን ከሂደት አንጻር ሳይሆን ውጤትን መሠረት ያደረገ ስልትን ቀይሶ በመሄድ አራአያነት ያለው ስራ በመስራት የሀገራችንን ከተሞች የብልጽግና ማሳያ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል ክብርት ሚኒስትር በማጠቃለያቸው፡፡

Posted in: ዜና