የካቲት 16, 2026

በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር፣ የቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ በቤት ልማት ዘርፍ በማተኮር የተዘጋጀውንና ታህሳስ 28/ 2018 ዓ.ም ጸድቆ ወደስራ የገባውን የቤት ልማት ፖሊሲ ከከተማ እስከ ፌዴራል በተናበበ አግባብ ለመተግበር የሚያስችል ስልጠና ለሚመለከታቸው የክልልና የከተማ አስተዳደር የዘርፉ አመራሮች እና ባለሙያዎች በዛሬው ዕለት በአዳማ ከተማ ሰጠ፡፡ መድረኩን የከፈቱትና የፖሊሲ ሰነዱን ያቀረቡት የቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚው አቶ ጸጋዬ ሙሼ በንግግራቸው ፖሊሲው በዋናነት በሀገራችን ዋና ዋና ከተሞች የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ የተለያዩ የቤት አቅርቦት ስልቶች ተነድፈው ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የወጣው የቤት ልማት ፖሊሲ ቀደም ሲል የነበረውን ገጠሩ ሲያድግ ከተማው አብሮ ያድጋል የሚለውን አስተሳሰብ የሰበረና በዝሃ-ኢኮኖሚን የተከተለ በመሆኑ ግብርናን ጨምሮ 5 ዘርፎችን በመለየት የከተሜነትን አይቀሬነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን መስራት የሚያስችል መሆኑ የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮችን ለማስፋት ዕድል የሚፈጥር መሆኑ ተብራርቷል፡፡ አቶ ጸጋዬ ፖሊሲው የግሉን ተሳትፎ የሚያሳድጉ አማራጮችን በመከተል የግሉ ዘርፍ ፋይናንስና ቴክኖሎጂን ይዞ እንዲመጣ በማድረግና መንግስት መሬትና መሠረተ-ልማትን አሟልቶ እንዲያቀርብ በማድረግ በተለያዩ የቤት ልማት አማራጮች የተገነቡ ቤቶችን በኪራይና በግል ይዞታነት በአማራጭነት ማቅረብ የሚቻልበትን ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡ ከቤት ልማት ፖሊሲው ቀጥሎ ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር በመጡ ተጋባዥ ዕንግዳ አንድ ዕቅድና አንድ ሪፖርትን የተመለከተ ስልጠና ተሰጥቷል። አንድ ዕቅድና አንድ ሪፖርት የተያዘውን ዓላማዎች ለማሳካት፤ ስራዎቻችንን በአግባቡ ለመተግበር፤ ዕቅዱ ሊያሳካቸው የሚገቡ ተግባራትን ለመለየት፤ የልማት ውጤትን ለማስተባበር፤ ውጤታማ የሆኑና ያልሆኑትን ለመለየት፤ ተቋማት እስከ ቀበሌ መዋቅር ተሳስረው እንዲሄዱ ለማድረግ፤ የእቅድና ውጤት መጣጣምን ለመፍጠር፤ ሀገራዊ የልማት ዕቅድ ግቦችን ለማሳካት፤ የተቋማት የተግባር አንድነትና ውጤትን ለማስተሳሰር፤ ሀገራዊ የልማት ግቦች ስኬትን ዕውን ለማድረግ፤ የሀብት ብክነትን ለመቀነስ፤ የተናበበ ዕቅድና የመንግስት ሀብት አመዳደብ እንዲኖር ለማድረግ፤ የተናበበ የልማት ፋይናንስ ማዕቀፍ እንዲኖር እና ከሪፎርም ጋር የተናበበ የሀብት አሰባሰብ እንዲኖር ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑ በስልጠናው ሂደት ተወስቷል፡፡ በመጨረሻም በቀረቡት የስልጠና ሠነዶች ላይ በተደረጉ ውይይቶች የጋራ አረዳድ ተይዟል፡፡

Posted in: ዜና