ታህሳስ 12, 2025

አዳማ፣ ህዳር 27/2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)

በኢትዮጵያ ላለፉት 20 ዓመታት የገጠር ወረዳዎችን ከአጎራባች ወረዳዎችና ከተሞች ጋር በተንጠልጣይ ድልድዮች በማገናኘት አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ከሌሎች ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር ፕሮጀክቱ በተተገበረባቸው አምስት ክልሎች 250 ተንጠልጣይ ድልድዮችን የሰራው መንግስታዊ ያልሆነው የልማት ድርጅት ሄልቬታስ ኢትዮጵያ ከሚኒስቴር መ/ቤቱና ከክልሎች ለተውጣጡ 25 የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና የምህንድስና ባለሙያዎች ለሁለት ቀናት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና የማጠናቀቅ እና በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ስር በሚገኘው ዊዝደም ኢንተርፕራይዝ የበለጸገው ሲስተም ርክክብ ተከናውኗል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የሀገራዊ መሠረተ-ልማት ቅንጅት መሪ ስራ አስፈጻሚው አቶ ቴዎድሮስ ተገኝ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የፕሮግራሙ ዋነኛ ዓላማ በልማት አጋር ድርጅቶች ትብብርና በዊዝደም ኢንተርፕራይዝ የበለጸገውን እና በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ባለቤትነት የሚተዳደረውን የተንጠልጣይ ድልድይ አሴት ማኔጅመንት ሲስተም ልማት ርክክብን ይፋ ማድረግ ሲሆን ሰልጣኞች በስልጠና ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተጨባጭ እውነት እንዲቀይሩት ከአደራ ጭምር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ አክለውም ስራውን ጀመርነው እንጂ አልጨረስነውም፡፡ ወደፊት የሚገጥሙንን ችግሮች በጋራ እየፈታን ሲስተሙን ዕውን እናደርጋለን ብለዋል፡፡

የዊዝደም ኢንተርፕራይዝ የጥናት ቡድን ዓባላትም ስለበለጸገው አሴት ማኔጅመንት ሲስተም ዝርዝር መረጃ በማቅረብ የለማው ሲስተም በስራ ላይ ውሎ የሚፈለገው ውጤት እስኪመጣ ድረስ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ጋር በቅርበትና በቅንጅት እንደሚሰሩ ገልጸው ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የሄልቬታስ ኢትዮጵያ የልማት አጋር ድርጅት ቡድኖችም ሲስተሙን እንዲለማ ከማስጠናት ጀምሮ በተንጠልጣይ ድልድይ ስራዎች ላይ ውጤታማ ስራዎችን በኢትዮጵያ መስራታቸውን ገልጸው የባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ ስልጠና ከመስጠት ጀምሮ ሲስተሙን ዕውን ለማድረግ የሚረዱ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን ግዥ ለመፈጸም ያደረጉትን ጥረት ገልጸው ከጎናቸው ለተሰለፉ የልማት አጋር ድርጅቶች ምስጋናቸውን በመግለጽ በሚኒስቴር መ/ቤቱ በኩል ፕሮጀክቶች በጊዜ የተገደቡ በመሆናቸው ክልሎችን በማስተባበር በ10 ዓመቱ በመንገድ ልማት ዘርፍ የተያዙ ዕቅዶች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡

በመጨረሻም የገጠር ልማት ትስስር ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም አስተባባሪው አቶ መሐመድአሚን አደም እንደገለጹት መንግስት ለመንገድ ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት ወደስራ የገባ መሆኑን ገልጸው በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 373 ተንጠልጣይ ድልድዮችን ለመስራት ዕቅድ እንደተያዘና ካለፈው ወደዚህ የተላለፉ 202 ተንጠልጣይ ድልድዮችም እንደሚገነቡ ገልጸው ስራው የሚተገበረው በክልሎች ስለሆነ እስካሁን በ5 ክልሎች ብቻ ተወስኖ የቆየው የተንጠልጣይ ድልድይ ግንባታ በሁሉም ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተፈጻሚ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ሲስተሙን ማልማቱ ጊዜን የወሰደ ቢሆንም ዛሬ ላይ ተጠናቆ ለማየት በመብቃታቸው መደሰታቸውን ገልጸው ለተባባሪ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበው ክልሎች በሚኖራቸው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲስተሙ ወደስራ እንዲገባ የራሳቸውን ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበው ወደፊት በሚዘጋጀው ሁሉአቀፍ የአቅም ግንባታ የስልጠና መድረክ በመሳተፍ ማህበረሰቡን እንዲያገለግሉ በአደራ ጭምር አሳስበዋል፡፡

Posted in: ዜና