መስከረም 10, 2026

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 5/2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር የስራ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር እና የትብብር ስምምነት የፊርማ ሥነ-ሥርዓት አካሄደ፡፡

ስምምነቱን የተፈራረሙት በሚኒስቴር መ/ቤቱ በኩል የመሬትና ካዳስተር መሪ ስራ አስፈጻሚው አቶ ብዙዓለም አድማሱ በመግቢያቸው ላይ እንደተናገሩት ስምምነቱ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ አካል እንደሆነና ሀገራዊ የመሬት መረጃዎችን በአንድ ቋት በማስተሳሰር የዜጎችን፣ የመንግስትን እና የባለሃብቱን ጥቅም ለማረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነና ይህም በሀገራችን የከተማ መሬት አስተዳደርና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞን ወደ ትልቅ ምዕራፍ የሚያሸጋግር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በማያያዝ ስምምነቱ የሀገራችንን የከተሞች የመሬት መረጃ ሥርዓት ለማዘመን፤ የካዳስተር ምዝገባዎችን ዘመናዊና አስተማማኝ ለማድረግ እንዲሁም የመሬት አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋና ግልጽ በማድረግ የታሰበውን አገራዊ ራዕይ ለማሳካት የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን ወክለው የተገኙት አቶ ቢኒያም አበባው በበኩላቸው ስምምነቱ የሲስተም ልማትን በማዘመን ዲጂታል ካዳስተርን ወደ ተቀናጀ ሁሉን አቀፍ ካዳስተር በማሳደግ ለሁሉም ከተሞች ለማድረስ ያለመ በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ስምምነቱ የመሬት ምዝገባን ዲጂታላይዝ በማድረግ የካዳስተር እድገት ደረጃዎችን ለማስጠበቅ፤ በዋናነትም ከህጋዊ እና ከፊዚካል ካዳስተር ወደ ተቀናጀ ሁሉን አቀፍ ካዳስተር የማሸጋገር ምዕራፍ እንደሆነና ይህም የንብረት ግብር አሰባሰብን ለማጠናከርና የከተሞችን የውስጥ ገቢ ለማሳደግ፤እንዲሁም የዜጎችን የይዞታ ዋስትና ለማረጋገጥ እና የንብረት መብትን ለማስከበር የሚረዳ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

Posted in: ዜና