የካቲት 5, 2026
አዲስ አበባ፣ጥር 25 ቀን 2018 ዓ/ም (ከመልሚ)
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከዘርፉ ተጠሪ ተቋማት ጋር በሁለተኛው ዙር የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የዝግጅት ምዕራፍ እንዲያደርጉ ከተመረጡ መ/ቤቶች መካከል አንዱ ነው። ከሐምሌ 22 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የሪፎርሙን የዝግጀት ምዕራፍ ስራዎች ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በዛሬው ዕለትም በተሰሩት ስራዎች ሪፖርት ላይ ውይይት ተካሄዷል፡፡
የመንግስት አገልግሎት እና አስተዳደር ሪፎርም የአሰራር ቅልጥፍና ለማምጣት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና ዘመኑ ከሚያራምደው የአስተዳደር ሳይንስ ውጤት መሠረት አገልግሎትን ለዜጎች ለማቅረብ የሠራተኛው የእውቀት፣ የክህሎት፣ የአስተሳሰብ፣ የሞራል፣ እና የባህሪ ክፍተቶች ለማስተካከል የሚሰራ ሪፎርም ነው፡፡
ሪፎርሙ በዋናነት ምቹ የስራ አካባቢን መፍጠር፣ የመንግስት አስተዳደርና አደረጃጀት ስርዓትን ማሳለጥ፣ የመንግስት ሰራተኛ የብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ስርዓት መገንባት የማስፈጸም አቅምን ማሳደግ፣ ዲጅታል ሲቪል ሰርቪስ በመገንባት ቅቡልነት ያላቸው አገልግሎቶች እና ውሳኔዎች ማቀላጠፍ፣ ብዝሃነትንና አካታችነትን ያረጋገጠ የሲቪል ሰርቪስ ግንባታ ማፋጠን፣ በዘርፉ ነፃና ገለልተኛ የተቋም ግንባታ ማሳለጥ እና የሲቪል ሰርቪስ ገቢር ነበብ አመራር እና የተቋም ግንባታ ማፋጠን የሚሉ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ ነው፡፡
እንደ ዘርፍ እነዝህን ዋና ዋና ጉዳዮችን ታሳቢ ያደረገ በእስካሁን ሂደት በዝግጀት ምዕራፍ የተሰሩ ስራዎችን ቀርበው ነው ውይይት የተደረገው፡፡
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የመሰረተ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር የትምጌታ አስራት(ዶ/ር) የሪፎርሙ የዝግጀት ምዕራፍ ስራዎች በዘርፍ አመራር እና በተዋቀረው ከሚቴ አማካይነት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ስራውን በውጤት አሁን ያለበት ደረጃ ማድረስ መቻሉን ገልጸው በቀጣይም ይሄው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡