ጥር 1, 2026

ቢሾፍቱ፣ ታህሳስ 15 ቀን 2018 ዓ/ም (ከመልሚ)

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የዘርፉ የ2018 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማኔጅመንት አባላት፣ የዘርፉ አመራሮች እና ባለሙያዎች እንዲሁም የተጠሪ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ነው የግምገማ መድረክ የተካሄደው።

መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ እንዳሉት የሚስቴር መስሪያ ቤቱ የዘርፉ የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት እቅድ አፈጻጸም የእያንዳንዱ ዘርፍ ምን አቅዶ ምን ተግብሯል የሚለውን እና ጠንካራ እና ደካማ ጎን በመለየት በቀጣይ ግማሽ ዓመት በትኩረት የሚሰራበት ይሆናል ብለዋል።

የከተማ ልማት ዘርፍ ከለውጡ መንግስት ወዲህ መንግስት ለከተማ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እና ከፍተኛ መነቃቃት የታየበት እንዲሁም በከፍተኛ የማንሰራራት ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል ።

የተቋማት፣ የስራ ክፍሎች፣ የአመራር እና የሲስተም ቅንጅት ትኩረት የሚገባቸው ጉዳዮች ሲሆኑ የመንግስት አገልግሎት እና አስተዳደር ሪፎርም በተለየ ትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል ክብርት ሚኒስትር ።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የከተማ አስተዳደር እና አገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ፈንታ ደጀን በከተማ አስተዳደር እና አገልግሎት ዙሪያ የመዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የከተሞች ፋይናንስና ገቢ ሪፎርም፣ የከተሞች ጽዳት እና አረንጓዴ ልማት አገልግሎት፣ የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም፣ የከተማ ፕላን እና አከታተም ስርዓት እና የከተማ መሬት አስተዳደር እና የካዳስተር ስርዓት በሚመለከት በግማሽ አመቱ የተሰሩ ስራዎች አቅርበዋል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቤቶች እና የከተማ ልማት ዘርፍ ሚስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሄለን ደበበ በበኩላቸው የቤት ልማት ፖሊሲ አስመልክቶ የከተሞች የቤት ልማት ፕሮግራም፣ የገጠር ቤት ልማት ፕሮግራም፣ የቤት መረጃና አስተዳደር ፕሮግራም፣ ቅንጅታዊ የመስክ ክትትል እና ድጋፍ እንዲሁም የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ስራዎችን በተመለከተ የዲዛይን ዝግጅት ስራዎች፣ በመንግሥት አስተባባሪነት የተገነቡ ቤቶች፣ በግሉ ዘርፍ የተገነቡ ቤቶች፣ የገጠር ማዕከላት የቤት ልማት፣ የቤት ልማት ፋይናንስ፣ የቤት መረጃ አስተዳደር፣ የሪል ፕሮፐርቲ ግብይት እና ግመታ ፣ የከተማ መሰረተ ልማት ስራዎች እና የአረንጓዴ መሰረተ ልማት እና የኮሪደር ስራዎች አፈጻጸም አቅርበዋል።

የመሰረተ ልማት ዘርፍ ሚነስትር ዴኤታ ክቡር የትምጌታ አስራት(ዶ/ር) በተመሳሳይ የዘርፉ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የፕሮጀክት አፈጻጸምን አስመልክተው የመንገድ ግንባታ አፈጻጸም፣ የመንገድ ጥገና አፈጻጸም፣ የወሰን ማስከበር ስራዎች አፈጻጸም፣ የካፒታል በጀት አጠቃቀም፣ የመንገድ ፈንድ የስድስት ወር የገቢ አፈጻጸም፣ የገጠር መንገድ ትስስር ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም፣ የተቋም ግንባታ፣ አጠቃላይ የሪፎርሙ ስራዎች፣ የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነት እና ውጤታማነት እና የኮንስትራክሽን ልህቀት እና መሰል የስራዎች አፈጻጸም አቅርበዋል።

በመጨረሻም በክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ የማጠቃለያ ሀሳብ እና የቀጣይ የስራ አቅጣጫ በመስጠት የግምገማው መድረክ ተጠናቆ በከተማው የመንገድ ፕሮጀክት ተጎብኝቷል።

Posted in: ዜና