መጋቢት 6, 2026

ኮምቦልቻ፣ የካቲት 25 ቀን፣ 2018 ዓ.ም (ከ.መ.ል.ሚ) የገጠር ማዕከላትንና የኮሪደር ልማትን አቀናጅቶ ለመስራት የሚያስችል የልምድ ልውውጥ በደቡብ ወሎ ዞን በቃሉ ወረዳ የጮሪላ የገጠር ቀበሌ ማዕከላትን መነሻ በማድረግ በኮምቦልቻ ከተማ ውይይት ተካሄዷል፡፡

በዚህ የልምድ ልውውጥ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሰት፣ የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት የስራ ሀላፊዎች በገጠር ማዕከላት ጉብኝትና ልምድ ልውውጥ ተሳትፈዋል፡፡

በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የቤቶች ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀጋየ ሞሼ በልምድ ልውውጥ መድረኩ ላይ እንደተናገሩት መንግሰት የከተማውም ሆነ የገጠሩ ማህበረሰብን ኑሮ ለማሻሻል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በተቀናጀ አሠራር የገጠር ማዕከላትንና የኮሪደር ልማትን ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የገጠር ማዕከላት ግንባታ ሽግግር ተበታትኖ ለሚኖረው አርሶ አደር በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ አስፈላጊ የሚባሉትን የመንግሰት አገልግሎቶችንና መሠረተ-ልማቶች በማሟላት ዜጎች ለኑሮ ምቹና ሳቢ በሆነ ጤናው ተጠብቆ በመንገድ፣ በውሃ፣ በመብራት፣ የከተማ ግብርና ፓኬጆችን አሟልቶ በመተግበር በዘመናዊ መንገድ ኑሮውን መምራት ማስቻሉ ፋይዳው እጅግ የጎላ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ጸጋየ አያይዘውም ይሄ መርሀ ግብር የገጠሩ ማህበረሰብ ወደ ከተማ ከመፍለስ ይልቅ በአካባቢው የስራ ዕድልን ፈጥሮ የቤት ባለይዞታ በመሆን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የካበተ ባህላዊ እሴቱን አስጠብቆ በአካባቢው የሥራ ዕድል ተፈጥሮለት የተረጋጋ ህይወት እንዲኖር ያስችለዋል ብለዋል።

የገጠር ቀበሌ ማዕከላት ከኮሪደር ልማት ጋር መቀናጀትን አስመልክቶ ከተሳታፊዎች የተነሱ ችግሮች የገጠር ማዕከላቱ ተገንብተው እንደተጠናቀቁ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት አለመቻላቸው፣ በተለይ ውሃ፣ መብራት፣ መንገድ፣ የጤና ቷማት ፣ ትምህርት ቤቶች ስታንዳርዳቸውን የጠበቁ አለመሆን፣ የሚገነቡት መሠረተ ልማቶች የህበረተሰቡን ባህልና እሴት የጠበቁ ሆነው ከመሄድ አንጻር ክፍተት መኖሩ፣ ለውጤታማነቱ ፈታኝ ስለሚሆን በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሰት በደቡብ ወሎ ዞን በቃሉ ወረዳ  የምትገኝ የጮሪሳ 06 የገጠር ቀበሌ የኮሪደርንና የገጠር ማዕከል በተሳታፊዎች ጉብኝት ተካሄዷል ፡፡

Posted in: ዜና