 
			ጥቅምት 15, 2025
ከተሞች ያላቸውን ልምድ የሚለዋወጡበት፣ አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ጥናቶችና ምርምሮች የሚቀርቡበት፣ የከተሞች ውጤታማ ስራዎች በኢግዚብሽን ቀርበው የሚጎበኙበት እንደመሆኑ የሰመራ ሎጊያ ከተማም እንግዶቿን ለመቀበል ሽርጉድ እያለች ነው፡፡
ከዚህ ቀደም የተካሄዱት የኢትዮጵያ የከተሞች ፎረም ዝግጅቶች የታለመላቸውን አላማ ከማሳካት አንፃር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበረከታቸው የሚታወስ ነው፡፡ በተለይ በየአመቱ መሻሻሎችን በማሳየት የዘርፉን ውጤታማነት ለማረጋገጥ በሚያስችል የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ በማተኮር ዝግጅቶች በመካሄዳቸው በከተማ ልማት ዘርፉ ላይ እየተደመረ የሚሄድ ውጤት መታየት ተችሏል፡፡
ይሄንኑ ዝግጅት ለመጎብኘት ወደ ሰመራ ሎጊያ ከተማ ያቀኑት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚ/ድኤታ እና የፎረሙ የአብይ ኮሚቴ ስብሳቢ ክቡር አቶ ፈንታ ደጀን ከክልሉ እና ከከተማው ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱም የሰመራ ሎጊያ ከተማ የአዘጋጅነቱን ኃላፊነት ከተረከበችበት ማግስት ጀምሮ ሰፊ ዝግጅት ስታደርግ መቆየቷ ተነስቷል።
አሁን ላይ ዝግጅቱን የክልሉ መንግስት ከከተማ አሰተዳደር ጋር በመቀናጀት እየሰራ ነው ያሉት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ሚኒስቴር መ/ቤቱ በቅርበት እያደረገ ያለውን ክትትል እና ድጋፍ አድንቀዋል በቀጣይ መሻሻል አሉባቸው ባሉዋቸው ጉዳዬች ላይ የሚኒስቴር መ/ቤቱን ድጋፍ ጠይቀዋል።
ክቡር ሚኒስትር ድኤታ አቶ ፈንታ ደጀን በበኩላቸው ክልሉ በልዩ ትኩረት ፎረሙ በተያዘለት ጊዜ እንዲካሄድ እና የኢትዮጵያ ከተሞች ወደ ክልሉ እንዲመጡ እያደረገ ስላለው ጥረት አድንቀዋል ያልተጠናቀቁ ስራዎችን በጊዜ የለኝም መንፈስ እንድሰራ በማሳሰብ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ከተሞች በፎረሙ ለመሳተፍ እየተመዘገቡ ነው፡፡ በፎረሙ 150 በ ከተሞች ከ10 በላይ ድርጅቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ፡፡
የከተሞች ምዝገባ የሚያበቃው መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ/ም ስለሆነ ያልተመዘገባችሁ ከተሞች ይህንን በመረዳት በአስቸኳይ እንድትመዘገቡ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ጥሪውን ያቀርባል።
 
			