ነሐሴ 28, 2025

ጅግጅጋ፣ ነሐሴ 20 ቀን 2017 ዓ/ም (ከመልሚ) የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ ክቡር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ የሶማሌ ክልል ፕሬዝደንት ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጨምሮ የፌዴራል እና የክልሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት 2ኛ ሀገር አቀፍ የመንገድ ዘርፍ ጉባኤ አካሄዷል።

የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ በመክፈቻ ንግግራቸው መንገድ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ ፈጣን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማትን ለማስቀጠል በተለይም የሀገራችን የመንገድ አውታር  ከተማን ከገጠር የተለያዩ የኢኮኖሚ ትስስርን የሚፈጥር እና በመካሄድ ላይ ያለውን ሁሉን አቀፍ ልማት ለማፋጠንና የአገሪቱን የብልጽግና ጉዞ በማፋጠን ረገድ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

የመንገድ ግንባታ በአገሪቷ ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው የመሠረተ ልማት ዘርፎች አንዱ ሲሆን እንቅስቃሴን እና ተደራሽነትን ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ ለማስኬድ አስችሏል ብለዋል ክቡር ፕረዚዳንት ሙስጤፌ።

በአጠቃላይ በመንገድ ግንባታ ላይ የፈሰሰው ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በዘርፉ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣ ሲሆን በፌደራል፣ በክልል፣ በከተሞች እና በወረዳዎች የተሰሩ መንገዶች ክረምት ከበጋ የሚያስኬዱ  እንደሆም ተናግረዋል።

በከተሞች እና በገጠር የሀገሪቱ ክፍል የሚካሄደው የኮሪደር ልማት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የተቻለ ሲሆን ፍትሐዊ የመሰረተ ልማት ስርጭት በማምጣት ረገድ የሶማሌ ክልል ተጠቃሽ መሆኗንም ገልጸዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒሰቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው መንገድ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ ፈጣን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማትን ለማስቀጠል እና አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብን ለመገንባት አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልፀዋል።

ባለፉት ዓመታት ተከታታይ የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራሞች ተቀርፀው ተግባራዊ በመደረጋቸው ውጤቶች መመዝገባቸው በተለይም የሀገራችን የመንገድ አውታር በከፍተኛ መጠን ያደገ ከመሆኑም በላይ ሀገራዊ የመንገድ መስረተ ልማት በከተሞች እና በገጠር ከሌሎች የልማት ሥራዎች ጋር ተመጋጋቢ ሆኖ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን ይህም በ10 ዓመቱ እቅድ እንደተመላከተው እንቅስቃሴን እና ተደራሽነትን ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ ለማስኬድ ማስቻሉንም ክብርት ሚኒስትር ተናግረዋል ።

በ2017 በጀት ዓመት በፌደራል ደረጃ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በኩል ብቻ ከ101 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የ1,048 ኪ.ሜ የአዲስ መንገዶች ግንባታ፣ የነባር መንገዶች ማጠናከር፣ ደረጃ ማሻሻል እና የከባድ ጥገና እንዲሁም የ10,926 ኪ.ሜ ወቅታዊ እና መደበኛ ጥገና በማካሄድ ከበጀት ዓመቱ የፊዚካል እቅድ 81 በመቶውን ማሳካት መቻሉን በቀረበው የዘረፋ ሪፓርት ተገልጿል ።

በአጠቃላይ በመንገድ ግንባታ ላይ የፈሰሰው ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በዘርፉ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣ ሲሆን በአገሪቱ ያለው ጠቅላላ የመንገድ ርዝመት በፌደራል፣ በክልል፣ በከተሞች እና በወረዳዎች የተሰሩ ክረምት ከበጋ የሚያስኬዱ መንገዶችን ጨምሮ አምና ከነበረበት 171,176 ኪሜ አሁን ላይ 180, 232 ሺ ኪ.ሜ መድረሱን፤ ከዚህ ውስጥ 30,824 ኪ.ሜ የፌደራል፣ 36,395 ኪ.ሜ የክልል፣ 44,717 ኪ.ሜ የከተማ እንዲሁም 68,297 ኪ.ሜ የወረዳ መንገድ ነው። ይህን ተከትሎም በ1000 ስኩዌር ኪ.ሜ ውስጥ ያለው የመንገድ ርዝመት 157 ኪ.ሜ የደረሰ ሲሆን ክረምት ከበጋ የሚያገለግል መንገድ ላይ ለመድረስ ዜጎች በአማካይ እንዲጓዙ የሚጠበቀው ርቀት 4.3 ኪ.ሜ መድረሱን። ከዚህም ባለፈ መንግሥት በክልሎች መካከል ፍትሃዊ የመንገድ ስርጭት እንዲኖር ትኩረት በመስጠት በተከታታይ ፍትሃዊነትን እንደ አንድ ዋና መመዘኛ ወስዶ እየተሰራ እንደሆነም ተነስቷል።

በመድረኩ ዘርፉን የሚመለከቱ ሰነዶች ቀርበው ውይይት በማድረግ በክብርት ሚኒስትሯ የማጠቃለያ ሀሳብ ተሰጥቶባቸዋል።

በ2017 በጀት አመት በመንገድ ዘርፍ የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው ክልሎች እና የከተማ አስተዳደር በመድረኩ ላይ የእውቅና መረሃ ግብር ተከናውኗል በዝህም የሶማሌ ክልል አንደኛ ደረጃ አፈጻጸም የሲዳማ ክልል ሁለተኛ ደረጃ አፈጻጸም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና የአፋር ክልል ሦስተኛ ደረጃ አፈጻጸም በማምጣት የዋንጫ እና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

ሪፖርተር: ኮከቤ ቢፍቱ
ፎቶግራፍ: አስመላሽ ተፈራ

Posted in: ዜና