ግንቦት 2, 2025

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24/2017 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)

ከግንቦት 11-15/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሚካሄደውን 20ኛውን የዓለም ስራ ድርጅት አህጉር አቀፍ ጉባኤን የተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ በዛሬው ዕለት ተሰጠ፡፡

በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የጋራ ጥምረት የተዘጋጀው 20ኛው የዓለም ስራ ድርጅት አህጉር አቀፍ ጉባኤ ጋዜጣዊ መግለጫ በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር በክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ የዓለም ስራ ድርጅት ካንትሪ ዳይሬክተር በሆኑት በሚስተር ካምቡላ ናዳባ እና በኢትዮጵያ ሠራተኞች ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር በክቡር አቶ ካሳሁን ፎሌ ተሰጥቷል፡፡

ይህ ኮንፈረንስ በየሁለት ዓመቱ አንድ ጊዜ የሚካሄድ አህጉራዊ ኮንፈረንስ ሲሆን በዋናነት የዓለም የስራ ድርጅት (ILO) እና ኮንፈረንሱን እንዲያዘጋጅ በተመረጠው ሀገር መንግስት በጋራ የሚዘጋጅ ነው፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ሚኒስትሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች፣ የማህበረሰብ ተወካዮች፣ የሲቪክና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የአሠሪዎች ፌዴሬሽን ተወካች፣ እንዲሁም የዘርፉ ምሁራንና ባለሙያዎች ይሳተፋሉ፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ኢትዮጵያ አዘጋጅ ሀገር ሆና እንድትመረጥ ካደረጓት ነገሮች መካከል የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከመሆኗ ባሻገር ለአረንጓዴ ልማት ስራዎች በሰጠችው ልዩ ትኩረትና በመንገድ መሠረተ-ልማትና በሌሎች ዘርፎች በተሰሩ ስራዎች፤ እንዲሁም ለአካባቢ ጥበቃና ለኮንፈረንስ ቱሪዝም አመች ሁኔታን ለመፍጠር እየተጋች ያለች ሀገር በመሆኗ ጭምር እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ጉባኤው ሀገራዊ መሠረተ-ልማት እንዲስፋፋና ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ከማገዙም በላይ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር፣ የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ፣ሰውና አካባቢ ተኮር የስራ ዕድል እንዲፈጠርና ኢንቨስትመንቱ እንዲሳብ በማድረግ የሚፈጠሩ የኢኮኖሚ ዕድሎች አሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ያግዛል፡፡
እንደ ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ገለጻ የሌበር ቤዝድ ፕራክክቲሺነርስ ኮንፈረንስ በዋናነት የሚያተኩረው ሀገራት በሚተገብሯቸው የተለያዩ የመሠረተ-ልማት እና ሌሎች ፕሮግራሞች ወይም ፕሮጀክቶች እንዴት የሰው ኃይልን በስፋት መጠቀም እንደሚችሉ፣ እንዴት ዘላቂና ጥራት ያለው የስራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል፣ እንዲሁም በሂደቱ የሠራተኞችን ዘላቂ ተጠቃሚነት እና ደህንነት ማረጋገጥ ስለሚቻልባቸው መንገዶች ነው፡፡

ጉበኤው ከሰው ሀብትና ከቴክኖሎጂ ጋር የተገናኙ ስራዎች የሚቀርቡበት፣ የመሠረተ-ልማትና ሌሎች ዘርፎች የሚፈልጉት ደህንነቱ የተጠበቀ የሠራተኛ ኃይል የሚፈጠርበት፣ የዜጎች የስራ ደህንነት የሚረጋገጥበት፣ ዘላቂነት ያለው ልማትና አካታችነት ዕውን የሚሆንበት ዕድል የሚፈጠርበት ነውም ብለዋል፡፡

ኮንፈረንሱ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ጨምሮ የዓለም የቴክኖሎጂ ዕድገት፣ ሠላምና ጸጥታ፣ የሀገራት የንግድ ፖሊሲዎች እና የአየር ንብረት ለውጥ በሠራተኞች ደህንነትና የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚኖራቸውን አዎንታዊ እና አሉታዊ ተጽዕኖዎች በመፈተሸ ስኬቶችን ይበልጥ ለማዳበር እና ለሚስተዋሉ ችግሮች የመፍትሄ ሃሳብ ለማፍለቅ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነው፤ ይህም ከዘላቂ የልማት ግብ ጋር የሚጣጣሙ፣ የአካባቢና ማህበራዊ ደህንነትን ታሳቢ ያደረጉና ሠፋፊ የስራ ዕድልን የሚፈጥሩ ኢንቨስትመንቶችን ይበልጥ ለመሳብ፣ ለማበረታታትና ለማስፋት ዕድሎችን የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

ከጉባኤ መድረኩ ባሻገር በሀገራዊ ፕሮጀክቶች፣ በኮሪደር ልማት፣ በቤቶች ልማት እና በሰፋፊ መሠረተ-ልማቶች ረገድ የተሰሩ ስራዎች በመስክ ይጎበኛሉ ሲሉም ክብርት ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለሺ ዘገዬ
የካሜራ ባለሙያ፡- ፈዬ ደሜ

Posted in: ዜና