መጋቢት 13, 2026

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1 ቀን 2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ) የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የቅዱሱን የረመዳን ወር ምክንያት በማድረግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የማኅበረሰባችን ክፍሎች የኢፍጣር መርሃ-ግብር ካዛንችስ በሚገኘው በወንድም ካሊድ ፋውንዴሽን ቅጥር ግብ ውስጥ በመገኘት ድጋፍ አደረገ፡፡

በመርሃ-ግብሩ ላይ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና የተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች፤ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት፤ እንዲሁም የወንድም ካሊድ ፋውንዴሽን የቦርድ አመራሮች፤ የፋውንዴሽኑ ሠራተኞች እና የኢፍጣር ተሳታፊ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በወንድም ካሊድ ፋውንዴሽን የደጋጎች እልፍኝ ጉብኝት የተደረገ ሲሆን በማዕከሉ 670 የሚሆኑ ኑሯቸውን በጎዳና ላይ አድርገው የነበሩ ወጣቶችና ህጻናት የተሰባሰቡበት ነው፡፡ “ጎዳና ችግኝ እንጂ ሰው የለውም!” የሚለውን መርህ አንግቦ የተነሳው ይህ ድርጅት በተለያየ ችግር ውስጥ ወድቀው ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን ተቀብሎ ከማስተናገድ ባለፈ የተረጅነት ስሜት እንዳያድርባቸውና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ በማሰብ የምግብና መጠለያ አገልግሎት ከማዕከሉ እያገኙ በኮሪደር ልማትና በሌሎች ፕሮጀክቶች በስራ ላይ ተሰማርተው የራሳቸውን የገቢ አቅም እንዲፈጥሩ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

ከጉብኝቱ በኋላ ሌሎች ኃይማኖታዊ ስርዓቶች ተከናውነው የኢፍጣር መርሃ-ግብሩ የከተከናወነ ሲሆን እሱን ተከትሎ ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ባደረጉት ንግግር ወንድም ካሊድ የተደላደለ ህይወቱን ትቶ መላ እሱነቱን ለዚህ ፋውንዴሽን አሳልፎ መስጠቱ ትልቅ ስብዕና መሆኑን በመግለጽ ከጎኑ ልንቆም ይገባል ብለዋል፡፡

ድጋፍ የሚደረግላቸው ዜጎችም ተረጂ ሆነው የሚቀጥሉ ሳይሆኑ ነገ ለሌሎች የሚተርፉ እንደሚሆኑ በመግለጽ ከተረጅነት ለመላቀቅ እያደረጉት ያለውን ጥረት በማድነቅ፣ ተስፋ ሳይቆርጡ ነገን የተሻለ ለማድረግ በርትተው መስራት እንዳለባቸው በመግለጽ በሚኒስቴር መ/ቤቱ ስም የተዘጋጀውን የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አበርክተዋል፡፡

የፋውንዴሽኑ መስራች ወንድም ካሊድ በበኩላቸው ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ከአሁን በፊት ማዕከሉን በድንገት ጎብኝተው ከሄዱ በኋላ የአምባሳደርነት ሚናን በመጫወት ባደረጉት ጥረት ፋውንዴሽኑ ከሁለት ሌሎች ተቋማት የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንዲያገኝ ማድረጋቸውን ገልጸው ዛሬ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ላደረገው ድጋፍ አክብሮትና ምስጋናቸውን በመግለጽ ይህም ለማዕከሉ ያላቸውን አጋርነት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

ሌሎች ተቋማት ይህን በመተዛዘን፣ በፍቅር፣ በአንድነት እና ማኅበራዊ ዋጋን ከፍ በማድረግ የሚከናወነውን የተቀደሰ ተግባር በማገዝ ረገድ አርዓያነት ያለው ተግባር በመሆኑ ሌሎች ተቋማትና ሁሉም ዜጋ አቅሙ በፈቀደ መጠን ከጎናቸው እንዲሰለፍ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Posted in: ዜና