ታህሳስ 22, 2025

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6 ቀን 2018 ዓ/ም (ከመልሚ)

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የሁለተኛው ዙር የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም በዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደሆነ ይታወቃል ፡፡ ይህንን ሪፎርም በተለያዩ ኮሚቴዎች ተዋቅሮ ስራ ላይ ያለ እና ከኮሚቴ ውጭ ያሉትን አመራሮች እና ሰራተኞች በበለጠ ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ መድረክ ነው፡፡

በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ፈንታ ደጀን እንደተናገሩት የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም እንደ ሀገር እየተሰራ ያለ ሪፎርም እንደመሆኑ በሁሉም ዘርፍ ላይ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣና በተለይ የከተማ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትኩረት በማድረግ ይሰራል ብለዋል ፡፡

ከተሞች ሰው ተኮር የሆነ እና የኢኮኖሚ ማዕከል በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጥን ዘመናዊና ቀልጣፋ ከማድረግ ጋር ተያይዞ በሁሉም ዘርፍ ላይ ተግባራዊ በማድረግ መንግስት ለከተሞች ትልቅ ትኩረት በመስጠት እየሰራ ሲሆን አገልግሎትን ግልጽ ከማድረግ ጋር ተያይዞ ስራ እና ሰራተኛ የሚያገናኝ ሪፎርም በመሆኑ ለሰራተኛው ግንዛቤ የሚፈጠርበት መድረክ እንደሆነ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ የመሰረተ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ የትምጌታ አስራት(ዶ/ር)እንዳሉት የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም አገልግሎት እና አስተዳደር ላይ ዓላማ ያደረገ ሪፎርም ሲሆን መንግስት ዜጎችን በከተሞች የሚስጡ አገልግሎቶች እርካታ እንዲኖራቸው፣ በየደረጃው ጉድለቶች እና ችግሮች እንዲቀረፉ ለማድረግ ነው፡፡

ጠንካራ፣ ገለልተኛ፣ ብቁ እና የሚሻገር ተቋም መፍጠር ማስፈለጉን እንደ አመራር እና ሰራተኛ ማወቅ፣ መገንዘብ መብትና ግዴታ በመሆኑ በእያንዳንዱ የሪፎርሙ ስራ ላይ በሂደቱ መሳተፍና በኮሚቴ ውስጥ ተደራጅተው የሚሰሩ አመራሮች እና ሰራተኞች በመደበኛ ስራቸው ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል

Posted in: ዜና