መጋቢት 4, 2026
ይርጋለም፣ የካቲት 24 ቀን 2018 ዓ/ም (ከመልሚ)
በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በሪል ፕሮፐርቲ ግብይት ግመታ እና ፈቃድ ዙሪያ ከሲዳማ ክልል፣ ከአራቱም ዞኖች፣ ከሐዋሳ እና ከይርጋለም ከተማ አስተዳደሮች ለመጡ የዘርፉ አመራሮች እና ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጠ።
ስልጠናው በሪል ፕሮፐርቲ ግብይት፣ ግመታ እና ፍቃድ ዘርፍ ሙያዊ እና የሕግ ማእቀፎች እንዲሁም በዘርፉ የተሰሩ ተሞክሮዎችም በዝርዝር የቀረበበት ነው።
የስልጠናው መድረክ በንግግር ያስጀመሩት የይርጋለም ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንባቆም ጴጥሮስ እንዳሉት መንግሥት በአሁኑ ሰዓት ያለውን ከፍተኛ የሆነ የከተማ ነዋሪዎች የመልማት ጥያቄ ለመመለስ የከተማ ገቢን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ለዚህ ደግሞ የሪል ፕሮፐርቲ ግብይት እና ግመታ ሥራዎችን በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ፎልቃ በበኩላቸው የሪል ፕሮፐርቲ ግብይት እና ግመታ ሥራ እንደ ሀገርም ሆነ በክልላችን ደረጃ አዲስ ዘርፍ በመሆኑ አደረጃጀቶችን በማጠናከር እና የሕግ ማእቅፎችን በማጽደቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለከተሞች ሁለንተናዊ ልማት መጠቀም እንደምገባ ገልጸዋል።
የሶማሌ ክልል የሪል ፕሮፐርቲ ግብይትና ግመታ ሥራዎች በተሞክሮነት ቀርቧል፣ በብዝኃ ግመታ፣ በቦታ ደረጃ እና በሕግ ማዕቀፎች ዙሪያ ስልጠና ተሰጥቷል።
በማጠቃለያውም በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የሪል ፕሮፐርቲ ግብይት ግመታ እና ፈቃድ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አዳነ ኧግዚ(ዶ/ር) እንዳሉት የሪል ፕሮፕርቲ ዘርፍ በዓለምም ሆነ ሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛውን የኢኮኖሚ ድርሻ የሚይዝ በመሆኑ መረጃ በማደራጀት እና አደረጃጀትን በመፍጠር ብሎም በሕግ በማስደግፍ ከዘርፉ የሚገኛውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማረጋገጥ እና አንድ ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር የተያዘውን ግብ ለማሳካት በየደረጃው ያለው አመራር እና ባለሙያ በቅንጅት እና በተነሣሽነት መስራት አለበት ብለዋል።
በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር እና በሌሎች ከተሞች ላይ እየተሰበሰበ ያለው የንብረት ሕጋዊ፣ አካላዊ እና ገበያ መረጃ መንግሥት ከንብረት ግብር እና ሌሎች ከንብረቱ ጋር የተያየዙ አገልግሎቶች ገቢ ለመሰብሰብ እና የከተሞች የመሠረተ ልማት አቅርቦት የበጀት ጉደለት ለማስተካከል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ዶ/ር አዳነ ተናግረዋል።