መጋቢት 10, 2026
አዳማ፣ የካቲት 26 ቀን 2018 ዓ.ም (ከመልሚ)
በከተማና መሠረተ-ልማት የሚኒስቴር የተዘጋጀ የተቋሙ ጥልቅ የዳሰሳ ጥናት፣ የተቋሙ የ10 ዓመት ፍኖተ-ካርታ ሠነድ እና የባለድርሻ አካላት ትንተና ሠነድ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መድረክ በዛሬው ዕለት በአዳማ ከተማ ተካሄደ፡፡
በተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የበላይ ኃላፊዎች፣ የሪፎርም ጥናት ቡድኑ ዐብይና የቴክኒክ ኮሚቴ ዓባላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
የውይይት መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሔለን ደበበ ባስተላለፉት መልዕክት እንደ ሀገር ለሪፎርም ስራ ትኩረት በመስጠት በሁሉም ዘርፍ አሁን ያለውን አሰራር ለመቀየር የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮችን ለመፍጠር እየተሰራ እንደሆነ ገልፀው የሪፎርም ጥናቱ በሚኒስቴር መ/ቤቱና በተጠሪ ተቋማት ቅንጅት በጋራ መጠናት ከጀመረ ካለፈው ሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ በሰባት ንዑሳን ኮሚቴዎች የተዋቀረው ቡድን የቅድመ-ዝግጅት ስራዎችን በጥሩ ሁኔታ በማከናወን በርካታ ተግባራትን ሲያከናወን በመቆየቱን ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም ከ2019 በጀት ዓመት ጀምሮ የተሟላ ቁመናን ፈጥሮ ለህብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል ቀሪ ስራዎችን በርብርብ ማጠናቀቅ እንደሚገባና በዛሬው መድረክም በቀረቡት ሠነዶች ላይ የማሻሻያ ግብአቶችን በመስጠት ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የእርሳቸውን መልዕክት ተከትሎ በመሠረታዊ የሪፎርም ማሻሻያ ስራዎች ላይ አጭር መግለጫ የሰጡት ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የተጋበዙት አቶ ተስፋዬ አጥሬ የሪፎርሙ አጠቃላይ አቅጣጫ የበቃ የሰው ኃይል በቦታው መድቦ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንደሆነ ተናግረው ዘርፉ የሚሰራው ስራ ከስታንዳርድ ጋር የተያያዘ ስለሆነ ስታንዳርዱን አስጠብቆ አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በመቀጠል ለዕለቱ የተዘጋጁ ሦስት የግንዛቤ ማስጨበጫ የስልጠና ሰነዶች በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የፖሊሲ፣ ስትራቴጂ እና የህግ ማዕቀፎች ዝግጅት ንዑስ ኮሚቴ ዓባላት ቀርበዋል።
በቀረቡት ሠነዶች ላይ የጋራ ውይይት ተደርጎ ከተወያዮቹ ሠነዶችን ለማዳበር የሚያስችሉ በርካታ ግብኣት የሚሆኑ ሀሳቦች ተነስተዋል።
ከቤቱ ለተነሱ ሀሳብና አስተያየቶች በሚኒቴር መ/ቤቱ የፓሊስና ስትራቴጂ ጥናትና ምርምር ሥራ አስፈጻሚና የጥናት ቡድኑ ሰብሳቢ አማን አሠፋ (ዶ/ር) ምላሽ በሚሹ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሔለን ደበበ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት ሠነዱ ቁልፍ ስትራቴጂክ ዶክመንት ስለሆነ ስራውን የሚሰራው ሰው ሠፊ ዕይታ ስለሚኖረው የተቋም ዳሰሳ ላይ በጥልቀት በማየት ጉድለቶች ታርመው ወጥነት ባለው መልኩ ምስል ከሳች በሆነ መንገድ መዘጋጀት እንደሚኖርበት አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡