መጋቢት 10, 2026
አዲስ አበባ፣ የካቲት 30/2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ) በፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስተባባሪነት የጠ/ሚ/ር ቤትና የፍትህ ሚኒስቴር በጋራ እያዘጋጁት ባለው የዳሰሳ ጥናት ዙሪያ የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማቱ ከፍተኛ አመራሮችና የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት በሚኒስቴር መ/ቤቱ አዳራሽ ግብአት ለማሰባሰብ የሚያስችል የመጀመሪያ ዙር የውይይት መድረክ ተካሄደ፡፡
በፕላንና ልማት ሚኒስትር በክብርት ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የተመራው መድረክ ዓላማ በተቋማት መካከል የሚነሱ የሚና መደራረቦችን በመለየት የመንግስት ሀብትን በውጤታማነት ከማሻሻል፣ እንዲሁም ሀገራዊ አደረጃጀቱ ከሀገራዊ የልማት ዕቅድና እየታዩ ካሉ ዘርፈ-ብዙ ለውጦች ጋር በተለይም ደግሞ ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ለውጦች ጋር የተናበበ እንዲሆን ለማድረግ ያለመ እንደሆነ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
በተደረገው የጋራ ውይይት ቀደም ሲል ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር በተላከው ቼክሊስት መሠረት በዘርፍ ደረጃ የተጠመረው መረጃ በክቡር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን ከቀረበ በኋላ በቼክሊስት ባልተካከተቱና ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባል በተባሉ ጉዳዮች ዙሪያ ተጨማሪ ሀሳቦችና ማብራሪያዎች በክቡራን ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ በተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና በሌሎች የስራ ክፍል ኃላፊዎች ቀርበው ሠፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በመጨረሻም ለፖሊሲ አቅጣጫዎች የሚሆኑና ለውሳኔ የሚያግዙ መረጃዎችን እንዳገኙና ተጨማሪ ውይይት የሚደረግባቸው መድረኮች እንደሚኖሩ ተገልጿል፡፡