ግንቦት 8, 2026

አዲስአበባ፣ ሚያዝያ 24/2018 ዓ.ም፣(ከመልሚ)

በስዊድን ኢምባሲ አዘጋጅነት ሚኒስቴር መ/ቤታችንን ጨምሮ በዘርፉ የተሰማሩ ዩኒቨርሲቲዎችና ከተለያዩ ሴክተር ተቋማት እንዲሁም ከግሉ ዘርፍ የተውጣጡ የፓናሉ ተሳታፊዎች የተገኙበት የፓናል ውይይት በአዲስአበባ አድዋ ሙዚዬም ተካሄዷል፡፡

ስዊድንና ኢትዮጵያ ያላቸውን 80 ዓመት ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር የእንጨት ውጤቶችን በኮንስትራክሽን ግብኣትነት ለመጠቀም የሚያስችል የስዊድን የልምድና የተሞክሮ ልውውጥ የታየበት የፓናል ውይይት ነው የተካሄደው፡፡

ይህን ሽግግር ዕውን ለማድረግ ተቀራርቦ መስራት እንደሚያስፈልግ የገለጹት አወያዩ እስካሁን ባለው ሁኔታ የእንጨት ምርቶችን ለኮንስትራክሽን ግብኣት የመጠቀም ልምዱ የዳበረ ባለመሆኑ የስዊድን ተሞክሮ በዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ ከ6 ተቋማት የተውጣጡ ተሳታፊዎች ልምድ የተጋሩበት ሲሆን እስካሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ ለአነስተኛ ግንባታ እንጨትንና የእንጨት ውጤቶችን ከመጠቀም ባለፈ በብዛት ጥቅም ላይ የማዋል ልምዱ የዳበረ እንዳልሆነና አብዛኛው የእንጨት ምርት ውጤትም ከውጭ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ በግሪን ሌጋሲ ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ውጤት አመርቂ በመሆኑ ይህን የደን ሽፋን ጥቅም ላይ በማዋል የሚጠበቀውን ውጤት ለማምጣት የስዊድንን ልምድና ተሞክሮ መውሰዱ ለዘርፉ ዕድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ በፓናል ውይይቱ ተነስቷል፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱን ወክለው የተሳተፉት የኮንስትክሽን ኢንዱስትሪ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚው ኢንጂ.ሙሉዓለም ደበበ በሀገራችን በተዘጋጀው የ10 ዓመቱ የልማት መሪ ዕቅድ ላይ 80 በመቶ የሚሆነውን የኮንስትራክሽን ግብኣት በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በተያዘው ዕቅድ መሰረት በፓሊሲ ማዕቀፉ ለእንጨት ውጤቶች ኮድና ስታንዳርድ ተዘጋጅቶላቸው እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህን በተመለከተ ስዊድን በዘርፉ የተሻለ ልምድና ተሞክሮ ያላት በመሆኑ የእንጨት ምርትን በግንባታው ዘርፍ 20 በመቶ ስለምትጠቀም ይህን ልምድ ወደ ሀገራችን አምጥተን ጥቅም ላይ ማዋል ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚለው ገዢ ሀሳብ ተወስዷል፡፡

Posted in: ዜና