የካቲት 24, 2026
አዳማ፣ የካቲት 14/2018 ዓ.ም ፣ (ከመልሚ )
ለሚኒስቴር መ/ቤቱ አመራርና ባለሙያዎች የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን በተቋም ደረጃ ለመተግበር በዝግጅት ምዕራፍ እየተጠኑ ካሉት አምዶች አንዱ በሆነው የዲጅታላይዜሽን አምድ ዙሪያ ወረቀት አልባ አሠራርን በተቋም ደረጃ እውን ለማድረግ እና አገልግሎትን ለማግኘት ባሉበት ቦታ ሆነው ቀጠሮ ለማስያዝ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ የተግባር ስልጠና ከሣይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር በመጡ አሰልጣኞች በአዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተሰጠ።
የስልጠና መድረኩን ተገኝተው በንግግር የከፈቱት የከተማና መሠረተ -ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ካሊድ አብዱራህማን ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ዕውን ለማድረግ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን በመግለጽ በተቋማችን በዝግጅት ምዕራፍ እየተጠኑ ካሉ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር የሪፎርም ጥናቶች መካከል አንዱ በሆነው የዲጂታላይዜሽን አምድ የለሙ ሶፍትዌሮችን ወደ ስራ ለማስገባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ስልጠና መውሰድ አስፈላጊ በመሆኑ የስልጠና መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸው ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ስልጠናውን በንቃት መከታተል ያስፈልጋል ብለዋል።
የእርሳቸውን የመክፈቻ ንግግር ተከትሎ በተሰጠ ስልጠና የደብዳቤ አስተዳደር ሥርዓታችን በቴክኖሎጂ የታገዘና ዘመናዊ እንዲሆን በማድረግ ከውጭ ወደ ተቋማችን የሚላክ ደብዳቤን፤ ከተቋማችን ወደ ሌላ ተቋም የሚላክን ደብዳቤ እና በተቋም ውስጥ ከአንድ የስራ ክፍል ወደሌላው የስራ ክፍል የሚደረግ የደብዳቤ ልውውጥን ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ አገልግሎቱን የተሳለጠና ደህንነቱ የተጠበቀ ለማድረግና ተገልጋዩ ከእንግልት በጸዳ መልኩ አገልግሎቱን እንዲያገኝ ለማድረግ ቴክኖሎጂው ያለውን ጠቀሜታና የአጠቃቀም ሂደቱን በተግባራዊ ልምምድና በተጨባጭ ማሳያዎች አሰልጥነዋል።
ሁለተኛው የስልጠና ርዕሰ-ጉዳይ ተገልጋዩ ባለበት ቦታ ሆኖ በተቋሙ አገልግሎቱን ለማግኘት ቀጠሮ የሚያሲዝበት ሥርዓት ነው። ይህም ምልልስን ለማስቀረትና ተገልጋዩን ተቀብሎ በማስተናገድ ሂደት በአገልግሎት ፈላጊውና በተገልጋዩ መካከል መልካምና ጤናማ ግንኙነትን ለመፍጠር እንዲሁም የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ የሚያስችል እንደሆነ የሚያሳይ የተግባር ልምምድ ተደርጓል።
በመጨረሻም የሚኒስቴር መ/ቤቱ ስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ አበራ አመንቴ በስልጠናው የተገኘው ዕውቀት ለስራችን አጋዥ መሆኑን ገልጸው ወደፊትም ከተቋሙ ጋር ያለን የስራ ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና በእኛ በኩል ማሟላት የሚገባንን ነገር አሟልተን መገኘት እንዳለብን የሚገልጽ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።