ጥር 22, 2026
አዲስ አበባ፣ ጥር 8/2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)
የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የዘርፉን ስትራቴጂካዊ ተልዕኮዎች በጥልቀት ለመወያየት እና ከዘርፉ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከር “አውደ-ሀሳብ በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር” በሚል መሪ ቃል የመጀመሪያ ዙር የውይይት መድረክ አካሄደ፡፡
አውደ-ሀሳብ በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ የዘርፉ
ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት መካከል የእውቀት ሽግግር ለማድረግ የታለመ
መድረክ ነው።
በመደመር ዕይታ ውስጥ የዘርፉን ተልዕኮ እና የወደፊት አቅጣጫዎች ላይ ጥልቅ ውይይት ተደርጎበታል ።
በመድረኩ ላይ ክብርት ሚኒስትሯ የሀሳብ ልዕልና ለሀገራዊ ለውጥና ዕድገት ያለውን አበርክቶ በተመለከተ የከተማና መሠረተ-ልማት ዘርፍ በመደመር መንግስት ዕይታ ውስጥ ያለውን ሚና ሲገልጹ እንደተናገሩት መድረኩ እስካሁን ከተደረጉት ውይይቶች ሁሉ የተለየ እንደሆነና ዛሬ የተጀመረውና በቀጣይ በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ አተኩሮ በየወሩ ተጠናክሮ የሚቀጥለው የውይይት መድረክ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ በማምጣት አይቀሬ የሆነውን የከተሞች ዕድገት ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጉዞ የምናፋጥንበት ነው ብለዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በማያያዝ ዓለም የሀሳብ ውጤት መሆንዋንና ግለሰቦች ያመነጩት ሀሳብ ወደ ሀገር፣ ተቋም እና ህዝብ ተሸጋግሮ ሀገራዊ የመፈጸም አቅምን ለማሳደግ እንደሚረዳና በክቡር ጠ/ሚ/ር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት የተቀረጹና ተጨባጭ ውጤት የታየባቸው ኢኒሼቲቮች ከለውጡ መንግስት በፊት የነበሩ አስተሳሰቦችን ሙሉ በሙሉ የቀየሩ መሆናቸውን በማሳያነት ገልጸዋል፡፡
መደመር በዘርፋችን እንዴት ሊገለጽ ይችላል፤ የመደመር መንግስት እይታስ ምን ይመስላል፤ ይህንን መሠረታዊ የዕይታ ለውጥ የተደረገበትን አስተሳሰብ ወደ መሬት ከማውረድ አንጻር ከማን ምን ይጠበቃል፤ የቅንጅት ክፍተትን ለመሙላት ምን መደረግ አለበት፤ ፕሮጀክቶችን በጥራት፣ በፍጥነት እና በተመጣጣኝ ወጪ ገንብቶ ለማጠናቀቅ የፕሮጀክት አስተዳደራችን ምን መምሰል
አለበት፤ በበጀት ዓመቱ የተያዙ ግቦችን ለማሳካት ምን እየተሰራ ነው፤ ምቹ የስራ አካባቢና ግንኙነትን ከመፍጠር አንጻር ምን መሰራት አለበት ይላሉ የሚሉና ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄዎች በአወያዩ ቀርበውላቸው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም በተደረጉ የጋራ ውይይቶች ከተወያዮቹ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ ከሰጡ በኋላ በማጠቃለያ አስተያየታቸው ከፖሊሲ ማዕቀፍ ዝግጅት ጀምሮ (ከአዲሱ የከተማ ልማት ፖሊሲ)፤ የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም እና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ ይዘዋቸው የሚመጡ ዕድሎችን አሟጦ ለመጠቀም የአመለካከት ለውጥ በማምጣትና ዘርፉን በቴክኖሎጂ በማገዝ መንግስት፣ የግሉ ሴክተር ተዋንያን፤የከተማ ነዋሪው እና መላው ህብረተሰባችን በጋራ ተደምረን፣ ተቀራርበን፣ ተባብረን እና የተሰጠንን ዕድል ተጠቅመን ዛሬ መስራት ያለብንን በሙሉ ዕምነትና በባለቤትነት ስሜት በመስራት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡