ጥር 27, 2026
ቢሾፍቱ ጥር 14 ቀን 2018 ዓ.ም (ከመልሚ) ኢትዮጵያ የከተሞችን የትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለማፋጠን የሚያስችል ታሪካዊ የከተሞች የሀብት ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ይፋ አደረገች
ብልጽግናዋ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን የመገንባት ራዕይ እውን ለማድረግ፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ የከተሞች ፕሮግራም መርሃ-ግብር የመግባቢያ ስምምነት ቢግ ዊን ፊላንትሮፒ (Big Win Philanthropy) ከተባለ አለም አቀፍ ተቋም ጋር (MoU) በይፋ ተፈራርሟል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ የከተሞች የሀብት ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር (Ethiopia Cities Resourcing Track) ይፋ ሆኗል።
በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ በአፍሪካ ፈጣን ከሚባሉት አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ የከተሞች መስፋፋት እንደ አንድ የኢኮኖሚ ምርታማነት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ምንጭ ተደርጎ መታየት እንዳለበት ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ ከተሞቻችን ለእነዚህ ተግዳሮቶች የሚሰጡት ምላሽ ውጤታማነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን የኑሮ ጥራት እና የኢኮኖሚያችንን የረጅም ጊዜ ተወዳዳሪነት ይወስናል ብለዋል።
የከተማ ሀብት ማሰባሰብ (Urban Resourcing): ከተሞች መሰረተ ልማቶችን እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን በራሳቸው የውስጥ ገቢ በነፃነት በገንዘብ እንዲደግፉ ማስቻል መሆኑን አስታውቀዋል።
የሀገር አቀፍ የንብረት ታክስ ማሻሻያ ዘመናዊ የንብረት ታክስ ሥርዓትን የአካባቢ ገቢ ማመንጫ መሠረት አድርጎ መዘርጋቱን ተናግረዋል።
እንደ አዲስ አበባ ያሉ ስኬታማ ከተሞችን አርአያነት በመከተል፣ በመላው አፍሪካ አህጉር የተሳካ የከተማ ትራንስፎርሜሽንን የሚያሳዩ ተጨማሪ አርአያ ከተሞችን ለመፍጠር አልመናል ሲሉ ክብርት ሚኒስትር ገልጸዋል።