ጥር 27, 2026

አዳማ፣ ጥር 16/2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)

በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር፣ በኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሥራ አስፈጻሚ አማካኝነት የተዘጋጀውና ትኩረቱን በድረ-ገጽ አጠቃቀም እና አስተዳደር ላይ ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ የህዝብ ግንኘነትና ኮሙዩኒኬሽን፤ እንዲሁም የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሰጥቷል፡፡

የስልጠና መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የተቋሙ የሥራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ፣ አቶ አበራ አመንታ የሁለቱ የስራ ክፍሎች ተግባር እርስ በርስ የሚደጋገፍና የሚናበብ በመሆኑ የመረጃ ባለቤት ለሆነው ህብረተሰብ ወቅታዊ፣ ተአማኒነት ያለው እና ፈጣን መረጃ ለማድረስ የሚደረገውን የመረጃ ቅብብሎሽ ጉዞ ማፋጠን ስለሚያስፈልግ ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ በየጊዜው ራስን እያበቁ መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ይህን ለማድረግ ደግሞ የአመራሩንና የባለሙያውን አቅም በየጊዜው እየፈተሹ መገንባት ስለሚያስፈልግ ከፌዴራል አስከ ከተማ ያለው መዋቅር ራሱን ዘመኑ ከደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ጋር አስተሳስሮ መጓዝ ስለሚያስፈልግ መድረኩ መፈጠሩ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ እንዲህ ዓይነት የግንኙነት አግባቦች በቀጣይም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

የእርሳቸውን ንግግር ተከትሎ ለዕለቱ የተዘጋጀው በተግባር የታገዘ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

በመጨረሻም በተደረገው የጋራ ውይይት ተሳታፊዎች እንዲህ ዓይነት የግንኙነት አግባብ መፈጠሩና በባለሙያ የታገዘ ስልጠና መሰጠቱ እንዳስደሰታቸው ገልጸው በቀጣይም ከአደረጃጀት ጀምሮ ብቃት ያለው የሰው ኃይል እስከማፍራት ድረስ ያለውን ክፍተት ለመሙላት መዋቅሩን በክትትልና ድጋፍ እስከ ማገዝ ድረስ ያለውን ስራ ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

Posted in: ዜና