መጋቢት 10, 2026
አዳማ፣ የካቲት 29፣ 2018 ዓ.ም (ከመልሚ) የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሴት አመራርና ሠራተኞች ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀንን (ማርች 8) በድምቀት አክብረዋል፡፡
የዘንድሮው የሴቶች ቀን (ማርች 8 ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ115ኛ ጊዜ በሀገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ ”የሴቶች ድምጽ እኩልነትና ለበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል ነው እየተከበረ ያለው፡፡
የከተማና መሠረተ-ልማት ሚነስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሔለን ደበበ ባስተላለፉት መልዕክት ሴቶች በተለያዩ ሀገራት ለሴቶች እኩልነትና ነጻነት ሲሉ በጽናት ታግለው ባስገኙት ድል በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፍ እኩል ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ብለዋል፡፡
ሴቶች ለራሳቸውም ይሁን ለሀገራቸው ለውጥና እድገት ተግተው መስራት እንዳለባቸው ገልጸው የትኛዉም ደረጃ ለመድረስ በእውቀት፣ በክህሎት እና በጽናት ራሳቸውን ለመለወጥ ብሎም በእስካሁን ዓመታት ውስጥ በሴቶች ድምጽ እንደሀገር ያልተፈቱ ችግሮችን ለመፍታት የሴቶችን መብት ለማረጋገጥ በቆራጥነት ተግተዉ መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል ክብርት ሚኒስትር ድኤታ ወ/ሮ ሄለን፡፡
በዓሉን አሰመልክቶ በገጠር መንገድ ትስስር ለምግብ ዋስትና ፕሮጀከት የሴቶችን ተጠቃሚነት አስመልክቶ ወ/ት መላት አናንያ ባቀረቡት ጽሁፍ በተለይ በቆላማ አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች የተሳለጠ መንገድ ባለመኖሩ ለትምህርት፣ በዕርግዝናና በወሊድ ወደጤና ተቋማት ለመሄድ፣ ውሃ ለመቅዳት ፣ያመረቱትን ምርት ወደገበያ ለማድረስ መንገድ የሚኖረው ፋይዳ እጅግ ጎላ በመሆኑ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በሚኒስቴር መ/ቤቱ የሴቶች ህብረት ሰብሳቢ ወ/ሮ ገነት ሐጎስ እንደተናገሩት በዓሉን ስናከብር ሴቶች ከወንዶች እኩል የመስራት፣ የመናገር፣ የመሰብሰብ እና ሌሎችም መብቶችን ለማስከበር መደራጀትና በጋራ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው ሴቶች ዛሬ ለደረስንበት ነጻነት ያጎናጸፉን ብዙ ጭቆናና ጫና ያንገሸገሻቸው ጥቂት ቆራጥ ሴቶች እ.አ.አ በ1990 የጀመሩት እጅግ መሪርና እልህ አስጨራሽ የትግል ውጤት ለማስቀጠል እንንደሆነ ተናግረዋል።
ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲወገዱ፣ ጾታዊ ጥቃቶችን መከላከል፣ ከጉልበት ብዝበዛ ነጻ እነዲሆኑ በህገ-መንግስቱ የተሠጡ መብቶች እውን እንዲሆኑ ሴቶች የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ወ/ሮ ገነት አደራ ብለዋል፡፡
በመጨረሻ ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ሔለን በመዝጊያ ንግግራቸው በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የሴቶችን ተሳታፊነት ለማረጋገጥና ሰላምን እንደሀገር ለማስጠበቅ የሚኖራቸውን ሚና እጅግ የጎላ ነው ብለዋል።