ታህሳስ 22, 2025

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3 ቀን 2018 ዓ.ም (ከ.መ.ል.ሚ) የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒሰቴር አመራሮችና ሠራተኞች የአለም የኤድስ ቀንን እና የጸረ-ጾታ ጥቃት ቀንን በተለያዩ መርሃ-ግብሮች አክብረዋል፡፡

የአለም ኤድስ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ38ኛ ጊዜ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ37ኛ ጊዜ “ተግዳሮቶችን በመቋቋም የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ምላሽን ዘላቂነት እናረጋግጥ” በሚል መሪ እንደሚከበር መልዕክት ያስተላፉት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አባድር ፋሪስ ናቸው፡፡

የጽ/ቤት ኃላፊው አያይዘው በአገራችን ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ቁጥር የሚሸፍኑትን ሴቶች ከሚደርስባቸው ጥቃት መከላከል፣ አቅማቸውን ማሳደግ እና ከኢኮኖሚ ጥገኝነት በማላቀቅ የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ኑሮ ለመለወጥም ሆነ የሀገራችንን የብልጽግና ጉዞ በማፋጠን ወደሚፈለገው የዕድገት ደረጃ ለመድረስ ሴቶች የራሳቸው የሆነ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

ሴቶች ጤናቸው የተጠበቀ፣ ሰላማቸው የተረጋገጠ፣ ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶቻቸው ሳይሸራረፉ ሊከበሩላቸው ይገባል ብለዋል አቶ አባድር።

የበዓሉ ዋና ዓላማ የፀረ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን እና ፆታዊ ጥቃት ቀን ምክንያት በማድረግ ለሚኒስቴር መ/ቤታችን አመራሮችና ሰራተኞች ግንዛቤ በመፍጠር የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ፈንድ ተጠቃሚ የሆኑ ህጻናት በተመለከተ ሪፖርት በማቅረብ በቀጣይ ወገናዊ አጋርነታችንን አጠናክረን ለመቀጠል እንደሆነ የገለጹት የጽ/ቤት ኃላፊው ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታን እና ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በስራ ቦታዎች ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ በሚመለከት ግንዛቤ በማሳደግ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ ውይይቶችን ለማካሄድ እንደሆነ የጽ/ቤት ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ የጸረ-ጾታ ጥቃት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደረጃ ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ ‹‹ጥቃትን የማይታገስ ማህበረሰብ ለትውልድ ግንባታ!!››በሚል መሪ ቃል ከህዳር 15-20 ቀን እንደሚከበር የገለጹት በሚኒስቴር መ/ቤቱ የስርዓተ-ጾታ እና አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃኑ ታደሰ ሲሆኑ፣ ጥቃትን በማስቆም በየደረጃው ያለ የመንግስት አካልና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና እንዲሁም ሕብረተሰቡ ጠንካራ አቋም በመያዝ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ስራ አስፈጻሚው አብራርተዋል፡፡

Posted in: ዜና