መጋቢት 6, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25/2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)

በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አዘጋጅነት በሌሎች ሚኒስቴር መ/ቤቶች አጋርነት እንዲሁም በባለድርሻ አካላትና በዘርፉ ተዋንያን ትብብርና ተሳትፎ ከሚያዝያ 9-12/2018 ዓ.ም ለ4 ቀናት በአዲስ አበባ አድስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል “ኢትዮጵያ ትገነባለች!” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደውን የኢትዮጵያ የመሠረተ-ልማትና ኮንስትራክሽን ሣምንት ዝግጅት በተመለከተ ከዘርፉ ተዋንያንና ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ውይይት ተደርጓል፡፡

በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ የተገኙት ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ባስተላለፉት መልዕክት  ኢትዮጵያ በመገንባት ሂደት ላይ ያለች ሀገር መሆኗን በመግለጽ ትልቅ የማደግ ፍላጎትና አቅም ያለን ከመሆናችንም በላይ ትኩረት ተሰጥቶት እያደገ ያለ ዘርፍ በመሆኑ የምንፈልገውን ሀገራዊ ለውጥ ለማምጣት የጋራ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

አያይዘውም በውይይቱ ለታደሙት አካላት ባለፉት 5 ዓመታት በተሰሩ ስራዎችና በተገኙ ውጤቶች የእናንተ እገዛና ተሣትፎ ሚናው ትልቅ ነው ካሉ በኋላ የተዘጋጀው ሁነት አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራ የሚከናወንበት፤ የገበያ ትስስር የሚፈጠርበት፣ የሀገር ውስጥ አምራቾችን አቅም የምናሳድግበት ሁነት ስለሆነ የጋራ ተሳትፎን ይጠቃል፤ ብለዋል።

የውይይቱ ዓላማም ይህን ትልቅ ሃገራዊ ሁነት በጋራ ለማዘጋጀት በምንችልበት ሁኔታ ላይ ለመነጋገር እንደሆነና ሀገራዊ ሁነት ስናዘጋጅ ዘርፉ የነበረበትን መጥፎ አተያይና ዝንባሌ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመቀየር ሀገርን በጋራ ለመገንባት የሚያስችል አቅምን ለመፍጠር ክብርት ሚኒስትር ተናግረዋል፡፡

ክቡር ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) በበኩላቸው ሁነቱ ስኬቶቻችንን ማሳየት ስለሆነ ውስጣዊ ጥንካሬያችንን ለማሳየት ተቋራጮች፣ አማካሪዎችና የግንባታ ባለቤቶች እንዲሁም የግንባታ ግብአት አምራቾች ተቀራርበው በመስራት አቅም ፈጥረው ከወትሮው በተለየ ዕይታ ለዘርፉ የሚሰጠውን ስም መቀየር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ 
 
የክቡር ሚኒስትር ዴኤታ ልዩ አማካሪ፣ በቀለ ንጉሰ (ዶ/ር) ለፕሮግራም ዝግጅቱ የተዘጋጀውን ዝርዝር ዕቅድ የሚገልጽ መረጃ የያዘ ሰነድ ቀርቦ የጋራ ውይይት ከተደረገና ከታዳሚዎች ለቀረቡ ሀሳብና አስተያየቶች ተገቢ ምላሽ ከተሰጠ በኋላ መድረኩ የመጀመሪያው እንደሆነና በቀጣይ ሌሎችንም የዘርፉ ተዋንያን ባሳተፈ መልኩ ቀጣይ መድረክ እንደሚኖር ተገልጾ የዕለቱ መርሃ ግብር ተጠናቋል፡፡ 

Posted in: ዜና