ታህሳስ 29, 2025

የዘርፉ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ዐብይ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት ከታህሳስ 1-8 ቀን 2018 ዓ.ም በተሠሩ የሪፎርም ጥናት ሠነዶች ዝግጅት ስራ ላይ፣ ስራው የደረሰበትን ደረጃ ለመገምገም የሚያስችል ውይይት አካሄደ፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱን ጨምሮ ሦስቱን ተጠሪ ተቋማት (የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርን፣ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩትን እና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣንን) ባካተተ የአራቱ ተቋማት የዐብይ ኮሚቴ ዓባላት በተገኙበት የአፈጻጸም ግምገማ የተደረገ ሲሆን በተደረገው የአፈጻጸም ግምገማ እስካሁን የተሰሩ ስራዎች በጥቅል ሲገመገሙ ሁሉም ተቋማት ተቀራራቢ በሆነ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆናቸው በቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል፡፡

በቀረበው ሪፖርት መነሻነት በተደረገው የጋራ ውይይት ስራው ከተቀመጠው ጊዜ አንጻር በታሰበው ፍጥነት እየሄደ ስላልሆነ ስራውን ለመረዳት የወሰደብንን ጊዜ ለማካካስ በሚያስችል ፍጥነት መጓዝ ይኖርብናል ሲሉ የዐብይ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር እና በተዋረድ ባለው መዋቅር እንዲተገበር የሚፈለገው የመንግስት አገልግሎት እና አስተዳደር ሪፎርም ለትግበራው ውጤታማነት ሠራተኛው፣ ባለድርሻ እና አስፈፃሚ አካላት በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው ለትግበራው ስኬት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፤ ለዚህም ያለውን ሪሶርስና የሰው ኃይል አቅም በሚገባ መጠቀም ስለሚያስፈልግ በዛ ልክ ጉዳዩን አስፍቶ ማየት እንደሚገባና ዕቅዶች በሣምንት ተሸንሽነው ሊዘጋጁና ሊተገበሩ እንዲሁም ስራው የደረሰበት ደረጃ በየሣምንቱ ሊገመገም እንደሚገባ በማስታወስ 9 ተተኳሪ ነጥቦችን የያዘ አቅጣጫም ተቀምጧል፡፡

Posted in: ዜና