ጥር 15, 2026

አዲስአበባ፡-ጥር 5 ቀን፣2018 ዓ.ም (ከ.መ.ል.ሚ)

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በክረምት በጎፈቃድ አገልግሎት መርሃ-ግብር ያስገነባቸውን የተቀናጀ ሞዴል የመኖሪያ መንደር ታህሳስ 29 ቀን 2018 ዓ.ም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በይፋ ተመርቀው ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል፡፡

ይህንን አስመልክተው የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ለተለያዩ ሚዲያዎች ጥር 5 ቀን 2018 ዓ.ም ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት እና በስሩ ከሚገኙ የተጠሪ ተቋማት ጋር በመተባበር 150 ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተቀናጀ ሞዴል የመኖሪያ መንደር በይፋ አስመርቆ ለተጠቃሚዎች ማስተላለፉን ክብርት ሚኒስትሯ አብራርተዋል፡፡

የተቀናጀ ሞዴል የመኖሪያ መንደር ለተጠቃሚዎች የተላለፉት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሰት በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ሰበታ ሀዋስ ወረዳ፣ በቱሉ አራራ ከተማ መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቅሰው ሞደል መንደሩ ለዜጎች ምቹ፣ ጽዱ፣ ለኑሮ ተስማሚ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ የተሟላላቸው፣ በኤሌክትሪክና በሶላር ኃይል የሚጠቀሙ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ የተሟላላቸው፣ የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ በዘላቂነት ለማሻሻል የከተማ ግብርናን የሚጠቀሙ፣ የምርትና የገበያ ሰንሰለትን ያካተተ የተቀናጀ አሰራር እንደተዘረጋላቸው ተናግረዋል፡፡

ከብርት ሚኒስትሯ አክለውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከዚህ በፊት በሀረር ከተማ፣ በመቀሌ እና በሰቆጣ በዝቅተኛ ኑሮ ለሚገኙ፣ አቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞች ሁሉም መሠረተ-ልማት የተሟላላቸው ቤቶችን አስገንብቶ ማስተላለፉን ገልጸዋል፡፡

የሀገሪቱ ዜጎች የሀገር ፍቅር እንዲኖራቸው፣ የኢትዮጵያን ባህልና እሴት ጠብቀው ከትውልድ ወደ ትዉልድ እንዲያስተላልፉ ሀብት ያለው በሀብቱ፣ እውቀት ያለው በእውቀቱ ከመንግሰት ጋር በመቀናጀት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ዜጎች ፍላጎታቸውን ማረጋገጥ በማስቻል የተሟላ የብልጽግናን ጉዞ ዳር ማድረስ ሁነኛው መንገድ ነው ያሉት ክብርት ወ/ሮ ጫለቱ በአዲስ አበባ የተጀመረውን ኮሪደር ልማት በሁሉም የሀገሪቱ ከተሞች ለማዳረስ በሚሠሩ ስራዎች በርካታ ዜጎች ደረጃውን የጠበቀ የመኖሪያ ቤት ባለቤት እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

Posted in: ዜና