ነሐሴ 17, 2026
ሐምሌ 27/2018ዓ.ም(ከመልሚ):- የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው በአንድ ጀንበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ታሪካዊ መርሃ-ግብር ላይ አሻራቸውን አኑረዋል።
ተቋማቱ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ወረዳ 03 ልዩ ስሙ ገበያ በሚባለው ስፍራ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተቀናጅተው ወደ ሀያ አንድ ሺህ የሚጠጉ የዛፍ ችግኞችን ተክለዋል።
በመረሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ አብዛኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ነዋሪ፥ በከተማ የሚኖር፤ ነገር ግን ከተሜነት ሊሰጠው ይገባ ከነበሩት ትሩፋቶች የራቀ ነበሩ። በዝቅተኛ ጥራትና እቅድ የተገነቡ፣ የተጨናነቁ፣ እልፍ ሲልም ለጎርፍና መሰል የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ተጋላጭ የሆኑ የመኖሪያ አካባቢዎች፣ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አሰባሰብና አወጋገድ ጉድለቶች እና አየር ብክለት ከተሞችን ለዜጎች ጤናማ እና ምርታማ ህይወት አመቺ እንዳይሆኑ አድርጓቸው ቆይቷል ብለዋል።
ክብርት ሚኒስትር አያይዘውም ላለፉት አምስት አመታት በተከናወኑ በአረንጓዴ አሻራ መረሀ ግብር በአረንጓዴና ተፋሰስ ልማት ፕሮጀክቶች ለከተሞች ሳንባ የሚሆኑ አረንጓዴ ቦታዎችን ማስፋፋት፣ ወንዞችን መታደግና የጎርፍ ተጋላጭነትን መቀነስ ተችሏል።
ከተሞች ከጥቅማዊ ፋይዳቸው ባለፈም የሥነ ውበት ዕሤትን የተጎናጸፉ፤ ለመኖር ምቹና ለእይታ ውብ እንዲሆኑ ተሠርቷል እየተሠራም ነው። በአረንጓዴ አሻራ ባለፉት 5 ዓመታት ብቻ ከ40 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለው 90% ማጽደቅ የተቻለ ሲሆን በዚህም የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በሀገር ዓቀፍ ደረጃ እ.አ.አ በ2018 ከነበረው 17.2% በእ.አ.አ በ2023 ወደ 23.6% አድጓል። የአዲስ አበባን የደን ሽፋን ብቻ ለይተን ብንመለከት እንኳን ከ11% ወደ 20% ደርሷል። እኚህና መሰል ፕሮጀክቶች የተፈጥሮ መልክዓ ምድሮች የከተማ ልማት ዕቅድ አንድ አካል ወደሆኑበት ሥነ ምኅዳራዊ (ecological) የከተማ ንድፍ እየተደረገ ላለው ሽግግር ሕያው ማሳያዎች ናቸው ብለዋል ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ።
የሚ/ር መስሪያ ቤቱ እና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኛ እና አመራር መላውን የከተማ ማህበረሰብ ባሳተፈ በመትከል ከተተከሉም በቀጣይነት እንክብካቤ ስራን በመስራት ለነዋሪዎቻቸው ምቹ እንዲሆኑ የማስቻል ራዕይን ከማሳካት ረገድ ትልቅ ሚና መጫወት አለብን ስሉ መልእክት አስተላልፈዋል ፡፡