ህዳር 13, 2026
አዲስ አበባ፣ ህዳር 2፣ 2019 ዓ.ም ( ከመልሚ) የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከአፍሪካ ልማት ባንክ የመንገድ ፕሮጀክት ኃላፊዎችና አስተባባሪዎች ጋር በሀገሪቱ በሚካሄዱ የመንገድ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር መሐመድ አብዱራህማን( ኢ/ር) እና የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች የተሳተፉ ሲሆን በአፍሪካልማት ባንክ በኩል ደግሞ የባንኩ የመንገድ ተራንስፖርት ኃላፊ ሚስተር ሪቻርድ ማሊና እና የዘርፉ ባለሙያዎች በውይይት መድረኩ ተሳትፈዋል፡፡
በመላው ሀገሪቱ እየተከናወኑ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች የደረሱበትን ደረጃ አስመልክቶ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከህዳር 2-12 ቀን 2026 ድረስ እያካሄደው የሚገኘውን ሱፐርቪዥን ስራ ከሚኒስቴር መስሪ ቤቱ ጋር የጋራ አረዳድ በመያዝ እያጋጠሙ የሚገኙ ተግዳሮቶችን በጋራ ተወያይቶ እልባት ለማስቀመጥ እንደሆነ በመድረኩ ተብራርቷል፡፡
በተለይ ትኩረት ተሰጥቶባቸው ውይይት የተካሄደባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች አንደኛው በኢትዮጵያ የተቀናጀ የመንገድ ትራንስፖርት ፌዝ አንድ የጅማ -ጭዳ፣ የሶዶ-ድንኬ ሳዉላ ፕሮግራም፣ ሁለተኛው ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ የኢትዮ-ጅቡቲ የኮሪደር ትራንስፖረት ፕሮጀክት የአዳማ አዋሽ ፈጣን የመንገድ ፕሮጀክት፣ ሦስተኛው ደግሞ የደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያ- የጅቡይቲ ኮሪደር ትራንስፖረት ፕሮጀክቶች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
ፕሮጀክቶቹ መቼ እንደተጀመሩ፣ ምን ያህል በጀት እንደተመደበላቸው፣ አሁን ላይ የደረሱበት ደረጃ፣ የተጠቀሙት በጀት፣ ሴቶችን ምንያህል ተጠቃሚ እንዳደረገ፣ የተከፈለ ካሳን አስመልክቶ በዝረዝር ቀርቦ እጋጠሙ የሚገኙ ችግሮችን መፍታት በሚያስችል ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተካሂዶ የጋራ አረዳድ ተይዟል፡፡