ነሐሴ 1, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17/2017 ዓ.ም፤ (ከመልሚ)

የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት አመራርና ሠራተኞች በ2018 በጀት ዓመት ሀገራዊ የልማት ዕቅድ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት አካሄዱ፡፡

መድረኩ በክብርት ሚ/ር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ተከፍቶ ሀገራዊ የልማት ዕቅዱን የተመለከተው ሠነድ በክቡር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጄን የቀረበ ሲሆን ሀገራዊ የልማት ዕቅዱ ከሀገራዊና ከዘርፉ የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምና ከዓለም አቀፍ ተጨባጭ ሁኔታው ጋር ተገናዝቦ የቀረበ ነው፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒን ጨምሮ የሚኒስቴር መ/ቤቱና የተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ሁሉም ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ዕቅዱ የ10 ዓመቱንና የ3 ዓመት ዕቅዱን መነሻ በማድረግ የተዘጋጀና በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ ተገምግሞ በየደረጃው ውይይት የተደረገበትና ስምምነት ላይ የተደረሰበት መሆኑን በመግለጽ ሀገራዊ ስዕል እንዲኖረንና የጋራ አረዳድ ይዘን ወደ ስራ እንድንገባ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሠነዱ በዋናነት ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ አዝማሚያዎችን መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ ሲሆን የማክሮ ኢኮኖሚ ዕቅድን፣ የኢኮኖሚ ዘርፎች ዕቅድን፣ የመሠረተ-ልማት ዘርፍ ዕቅድን፣ የማህበራዊና የህዝብ አገልግሎት ዕቅድን፣ የሠላም፣ የፍትህ እና የዲፕሎማሲ ዕቅድን ማዕከል አድርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡

በሠነዱ ውስጥ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች የተለዩ ሲሆን በቀጣይነት የገቢ አቅምን ማጠናከር፤ ውጤታማ የፋይናንስ ሥርዓትን መከተል፤ ውጤታማ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደርን ዕውን ማድረግ፤ የንግድ ጦርነት አሉታዊ ተጽዕኖዎችን መከላከል፤ አካታችና ውጤታማ ፋይናንስን ለአምራቾች ማቅረብ፤ አዳዲስ የትራንስፖርት አማራጭ ዘዴዎችን መከተል እና በተለዩት አምስት የኢኮኖሚ ዘርፎች ማለትም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና በዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ አተኩሮ መስራት፤ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ግብኣትን ማረጋገጥ፣ እንዲሁም ሌሎች ለተያዘው ግብ ስኬት የሚረዱ አማራጮችን መከተል እንደሚያስፈልግ በዕቅዱ ላይ ተመላክቷል፡፡

የቀረበውን ሠነድ ተከትሎ ከተወያዮቹ ግልጽነትን የሚሹ በርካታ ጥያቄና አስተያየቶች ቀርበው ለተነሱ ጥያቄዎች በክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ እና በክቡራን ሚኒስትር ዴኤታዎች የተብራራ መረጃ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በመጨረሻም ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት መድረኩ የተጠናቀቀ ሲሆን በማጠቃለያ ንግግራቸውም ኢትዮጵያ በማንሰራራት ላይ ያለች ሀገር መሆኗን በማስታወስ በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ እንድንነጋገር የስቻለን በሀሳብ ጥራት ላይ ማተኮራችን በመሆኑ ህዝቦቿ ተጋግዘን እና ተሰናስለን መስራታችን ዛሬ ለደረስንበት ደረጃ አብቅቶናል፡፡ ጊዜያዊ ፍላጎት ላይ መሰረት ያላደረገ መራር ውሳኔን የሚወስን መንግስትና ፓርቲ ስላለንና የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ በስርዓት ስለተመራ ውጤት ማምጣት ችለናል፡፡

በቀጣይም ሀገርን ከራስ ፍላጎት በላይ በማስቀደምና ብዝኃ የኢኮኖሚ አማራጮችን በመከተል በኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን ተቋቁሞ ለማለፍ የሁላችንንም ተሳትፎና ጥረት ስለሚጠይቅ በ2017 በጀት ዓመት ዓለም አቀፉን ጫና ተቋቁመን በሁሉም ረገድ ያስመዘገብናቸውን አመርቂና ተጨባጭ ውጤቶች ለማስቀጠል የመንግስትና የህዝብ ትስስርንና ሁለንተናዊ አጋርነትን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባናል ብለዋል፡፡

ሪፖርተር ፡- ስለሺ ዘገዬ
ፎቶግራፍ ፡- ፈዬ ደሜ

Posted in: ዜና