ነሐሴ 5, 2025

አዳማ፣ ሐምሌ 28/2017 ዓ.ም (ከመልሚ)

በፌዴራል መንግስትና በዓለም ባንክ ድጋፍ በተመረጡ ከተሞች ለመተግበር በተመደበው በጀት የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎችን ከተረጅነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር የተጀመረው የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔትና የሥራ ፕሮጀክት በ2017 በጀት ዓመት የተከናወኑ ስራዎችን በመገምገም የታዩ ድክመትና ጥንካሬዎችን ለይቶ በ2018 በጀት ዓመት እንደ ሀገር በዕቅድ የተያዙ ስራዎችን ለማከናወን የተዘጋጀውን ዕቅድ የጋራ ለማድረግ የተዘጋጀው መድረክ በዛሬው ዕለት በአዳማ ከተማ በኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር በይፋ ተጀምሯል፡፡

የፌዴራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደሮች የሥራ ኃላፊዎችና የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች የተሳተፉበትን ይህን መድረክ በክብር እንግድነት ተገኝተው በይፋ ያስጀመሩት የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ፣ ክቡር አቶ ፈንታ ደጀን በመክፈቻ ንግግራቸው ፕሮጀክቱ ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ ውጤታማ በመሆኑና የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች ከራሳቸው አልፎ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን በማመን መንግስት ፕሮጀክቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ያደረገ በመሆኑ ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ በብርቱ መትጋት እንደሚያስፈልግና የፕሮጀክቱ የመጨረሻ ግብ የሆነውን ተጠቃሚዎችን ውጤታማ የማድረግ ስራም ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ በ2018 በጀት ዓመት የሚሰሩ ስራዎች የዜጎችን ተደራሽነት የሚያሰፉ እንዲሆኑ ከወትሮው በተለየ ተነሳሽነት፣ የዓላማ አንድነት እና የተልዕኮ ስኬት መሰራት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የአዳማ ከተማ ስራ አስኪያጅ ክቡር አቶ ሀብታሙ ግዛው በበኩላቸው በ13 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተከተመችው የአዳማ ከተማ በአሁኑ ሰዓት 54 ሄክታር የቆዳ ስፋት እንዳላት ገልጸው በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ብቻ ከ5,996 በላይ ፕሮጀክቶችን ማስመረቅ መቻሉንና በኮሪደር ልማት ለተነሱ ዜጎች ከተማ አስተዳደሩ በመደበው በጀት 810 አባወራዎችን ማስተናገድ የሚችል 27 ብሎክ ያለው የባለ 5 ፎቅ የመኖሪያ ህንጻዎችን ገንብቶ ለርክክብ ዝግጁ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ለተሞክሮነትም ልምድ የሚወሰድባቸውን ፕሮጀክቶች የመድረኩ ተሳታፊዎች ተዘዋውረው እንዲጎበኙ ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የተሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች የተጎበኙ ሲሆን በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሆኑ ስኬታማ ሰዎች በመድረኩ ላይ ተገኝተው የስኬት ልምዳቸውን እንዲያጋሩ ተደርጓል፡፡

መድረኩ ለቀጣይ ቀናትም የሚቀጥል ሲሆን የሁሉም ክልሎች የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርቶች፤ በበጀት ዓመቱ የተደረጉ የመስክ ክትትልና ድጋፍ ሪፖርቶች፤ የ2018 በጀት ዓመት የፕሮጀክቱ መነሻና ታሳቢ ጉዳዮች፤ የፌዴራል፣ የክልል እና የከተሞች ዕቅድ ዝግጅት እና የማናበብ ሥራዎች እንዲሁም የክልሎች የፕሮጀክቱ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ከቀረበ በኋላ የማጠቃለያ ውይይትና ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚቀርቡ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለሺ ዘገዬ
የካሜራ ባለሙያ፡- አስመላሽ ተፈራ

Posted in: ዜና