ሰኔ 24, 2025

በበጀት ዓመቱ 634 የከተማ መሬት፣ ፕላን እና ፋይናንስ ዘርፍ ባለሙያዎች በዩኒቨርስቲዎቹ ስልጠና በመውሰድ የተመዘኑ ሲሆን አብዛኞቹ ባለሙያዎች ምዘናውን በስኬት ማጠናቀቃቸው ተገልጿል።

በመድረኩ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮቾ የተወጣጡ የዘርፉ አመራሮች እና በስልጠናው ወቅት ሲያስተባብሩ የነበሩ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

በማጠቃለያ መርሀግብር ላይ መልእክት ያስተላለፉት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚ/ዴኤታ ክቡር አቶ ፈንታ ደጀን በመሬትና ፕላን ዘርፍ የሀገሪቱን ከተሞች ችግር በሚፈታ መልኩ ስልጠናና ምዘና መካሄዱን ተናግረዋል።

ስልጠና በራሱ ውጤት ሳይሆን ውጤት ማምጫ መንገድ ነው ያሉት አቶ ፈንታ ይሄንን መሰረት በማድረግ የመሬት ስራችን ፈታኝ የነበረ ሲሆን አሁን መሻሻሎች አሉ ይሄም የስልጠናው ውጤት እንደሆነ አንስተዋል።

የከተሞች ገቢ ሪፎርም ፕ/ጽ/ቤት በከተሞች የገቢ አሰባሰብ ስርዓት በማሳደግ ከተሞች ወጪያቸውን ለመሸፈን የሚያስችል ደረጃ ለማድረስ በርካታ ስራዎች ሰርተው ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል ሚ/ዴኤታው።

በመድረኩ በ2017 በጀት አመት በአምስት ዩኒቨርስቲዎች ሲካሄድ የነበረው የከተማ መሬትና ፕላን ዘርፍ የስልጠናና ምዘና አፈጻጸም አጠቃላይ ሪፖርት እና የስልጠናና የምዘና የፋይዳ ጥናት ቀርበው ውይይት ተካሄዷል።

በመጨረሻም ከተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ተነስተው በክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የማጠቃለያ ሀሳብ በመስጠት እና በስልጠናና ምዘና ስራው ላይ ድጋፍ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት የእውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

ሪፖርተር : ኮከቤ ቢፍቱ
ፎቶግራፍ: ፈዬ ደሜ

Posted in: ዜና