ታህሳስ 22, 2025
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8 ቀን 2018 ዓ/ም (ከመልሚ)
በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የገጠር መንገድ ትስስርና ተደራሽነት ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የፕሮግራሙን የ2018 በጀት ዓመት የአራት ወራት እቅድ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ አካሄዷል፡፡
በመድረኩ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ መስተዳድሮች የተወጣጡ የዘርፉ አመራሮች እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
ፕሮግራሙን በንግግር ያስጀመሩት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) እንዳሉት የዛሬው የገጠር መንገድ ትስስርና ተደራሽነት ፕሮግራም የአራት ወራት እቅድ አፈጻጸም ስንገመግም በስራው ላይ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል እና ችግሮችን በመለየት እንዲሁም በቀጣይ በበጀት ዓመቱ የታቀዱት እቅዶች ለማሳካት የሚረዳ ነው ብለዋል።
ባለፈው የሰራ ጊዜያት በከተማ ልማት፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ እና በግብርና ዘርፎች በርካታ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን የገጠር ትስስር መንገድ የግብርና ግብዓትን እና ምርትን ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ የማይተካ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
አብዛኞቹ በክልሎች ካለን የመንገድ አውታር ውስጥ የተሰራው የገጠር መንገድ ሲሆን በቀጣይ ጊዜያትም በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎሜትሮች እንደሚሰሩ እንዲሁም የተለያዩ የሀል አማራጮችን በመጠቀም የአካባቢውን ሀብት መሰረት ባደረገ መልኩ የገጠሩን የአኗኗር ዘይቤ መቀየር ያስፈልጋል በማለት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘው ተናግረዋል።
የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የአራት ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የገጠር መንገድ ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዌስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ ፕሮግራሙ የ2017 በጀት ዓመት እና የ2018 በጀት ዓመት የአራት ወራት የእቅድ አፈጻጸም እና የእየክልሎቹ ጠቅለል ያለ ሪፖርት አቅርበዋል።
በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ከተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ቀርበው ውይይት በማድረግ በሚኒስትር ዴኤታው የማጠቃለያ ሀሳብ የዕለቱን መርሀ ግብር ተጠናቋል።