ሐምሌ 8, 2026

ቢሾፍቱ፣ ሰኔ 27/2018 ዓ.ም፣ (ከመልሚ)
የገጠር ትስስር እና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም የፌዴራል ቴክኒክ ኮሚቴ ዓመታዊ ጉባኤ በ2018 በጀት ዓመት የፕሮግራሙ አፈጻጸምና በ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ በቢሾፍቱ ከተማ ተወያይቷል፡፡

ከከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ እንዲሁም በቴክኒክ ኮሚቴ ዓባልነት ከተካተቱ በፌዴራል ደረጃ ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ ከታቀፉ ተቋማት የተውጣጡ አካላት  የተሳተፉበትን መድረክ የመሩት የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) እንደተናገሩት አጠቃላይ ካለው ሀገራዊ ሁኔታና የመልማት ፍላጎት አኳያ ፕሮግራሙን ለማጠናቀቅ ከዓለም ባንክ ጋር የተገባው ውል 5 ዓመት ቢሆንም ከዚያ ባጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ ባለን ፍላጎት መሠረት በዚያ ልክ አቅደን ወደ ስራ የገባን ስለሆነ የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸማችንን ስንገመግምና ቀጣይ ዕቅዳችንን ስናዘጋጅ ዙሪያ መለስ ዕይታ ኖሮን በፕሮግራሙ ትግበራ የገጠሙንን ማነቆዎች ፈትሸንና የመፍትሄ አማራጮችን አስቀምጠን በጥልቀት ልንወያይ ይገባል ብለዋል፡፡

የእርሳቸውን ንግግር ተከትሎ የበጀት ዓመቱ የአፈጻጸም ሪፖርትና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ በገጠር ትስስርና ተደራሽነት ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊው በአቶ መሀመድአሚን አደም ቀርቧል፡፡ 

እንደ አቶ መሀመድአሚን ገለጻ በተሰጡ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችና የተሸከርካሪ፣ የሞተር ሳይክል እና የአይቲ መሣሪያዎች ድጋፍና ፕሮግራሙን ለማስፈጸም በተፈጠሩ ተቋማትና አደረጃጀቶች በተሰሩ ስራዎች በበጀት ዓመቱ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር አዲስ መንገድና ከ3 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ጥገና ስራዎች በ126 የሀገሪቱ ወረዳዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህም አብዛኛውን የገጠሩን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
 
ፕሮጀክቱ ያስገኛቸውን ጠቀሜታዎች በተመለከተም የግብርና ምርት ሳይበላሽ ወደ ገበያ  ለማድረስ፤ ወላዶች በፍጥነት ወደ ጤና ተቋማት እንዲደርሱ ለማድረግ እና ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ሳይጉላሉ እንዲደርሱ ለማድግ ከማስቻሉም በላይ የመጠጥ ውኃን በቅርበት ለማግኘትና ለዜጎች የስራ ዕድልን በመፍጠር ረገድ የራሱ የሆነ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ገልጸዋል፡፡

የገጠሩን ማህበረሰብ በገበያ ለማስተሳሰር የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሶፍትዌር ልማት ጥናት ሰነድም ቀርቧል፡፡ ይህም የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር የገጠሩን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የገበያ መረጋጋትን ለመፍጠር የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በቀረቡ ሠነዶች መነሻነት በተደረገ የጋራ ውይይት የተለያዩ ጥያቄና አስተያየቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በመጨረሻም ክቡር ሚ/ር ዴኤታው በሰጡት ማጠቃለያ  ፕሮጀክቱ አዲስ እንደመሆኑ  የተሰሩ የቅድመ-ዝግጅት ስራዎች የወሰዱትን ጊዜ ለማካካስ በሚያስችል ሁኔታ ወደፊት መሻሻል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸው በቀጣይ የተናበበና የተቀናጀ የጋራ ርብርብ ማድረግን የሚጠይቅ ስለሆነ ይህን ታሳቢ በማድረግ የቀረበው ሪፖርት የተሰጡ ማሻሻያዎችን አካቶ በክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ለሚመራው ስቲሪንግ ኮሚቴ እንዲቀርብ በዓባላቱ ተወስኗል፡፡

Posted in: ዜና