ሐምሌ 27, 2026
ቢሾፍቱ፣ ሐምሌ 3 ቀን 2018 ዓ/ም (ከመልሚ) በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም የ2018 በጀት ዓመት የፕሮግራሙ አፈጻጸም እና በ2019 በጀት ዓመት እቅድ ላይ የፈደራል ስትሪንግ ኮሚቴ በቢሾፍቱ ከተማ የውይይት መድረክ አካሄዷል።
በመድረኩ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር እና የፌዴራል ስትሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒን ጨምሮ የስትሪንግ ኮሚቴ አባላት እና ከሁሉም ክልሎች እና ከድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር የመንገድ ዘርፍ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር እና የስትሪንግ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም ከአለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ እና ከክልሎች የጋራ መዋጮ በማድረግ የገጠሩን ማህበረሰብ ፍትሐዊ ተጠቃሚ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን የሚያጠናክር የትራንስፖርት አገልግሎትን በመስጠት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለ ፕሮግራም ነው።
በፕሮግራሙ በ2018 በጀት ዓመት ከታቀደው እቅድ አንጻር የነበሩ ጠንካራ ጎኖች እና ያጋጠሙ ችግሮችን የምንገመግምበት እንዲሁም በ2019 በጀት ዓመት የተለየ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራበት የጋራ ውይይት የምናካሄድበት መድረክ ነው ብለዋል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ፕሮግራም ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ መሀመድአሚን አደም የፕሮግራሙ የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ የተጠልጣይ ድልድይ የእግረኛ መንገድ፣ አዲስ የመንገድ ግንባታ፣ የኮንትራክተር እና የአማካሪ መረጣ፣ ስፔሻል ስትራክቸር እና ሌሎች በርካታ ስራዎች ላይ መሰራቱን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በበጀት ዓመቱ 11.3 ሚሊየን የገጠሩን ማህረሰብ ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን 50 በመቶ ሴቶች እንደሆኑና ፕሮጀክቱ በ12 ክልሎች እና በድሬድዋ ከተማ መስተዳድር ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በፕሮግራሙ በበጀት ዓመቱ 97,650 በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ የስራ እድል የተፈጠረና ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ ተቋማት እና ከሌሎች ፌዴራል ተቋማት ጋር አብረው በመቀናጀት እንደሚሰሩ በመግለጽ በቀጣይ በጀት ዓመት በርካታ ስራዎች ለመስራት በእቅድ እንደተያዘ ገልጸዋል።
በመድረኩ በርካታ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን በክብርት ሚኒስትር ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
በማጠቃለያውም ክብርት ሚኒስትር የፌዴራል ስትሪንግ ኮሚቴ ፕሮጀክቱን ወደ ፊት ለማስኬድ ከፍተኛ ድርሻ አለው። ፕሮጀክቱ ውጤታማ የሆነና የገጠሩን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ያደረገ መንገድ የሚሰራ ከመሆኑም በላይ በመንግስት ደረጃም ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ፕሮጀክት በመሆኑ በልዩ ትኩረት መስራት እና ውጠታማ ማድረግ ይገባል ብለዋል።