ጥር 15, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 4 ቀን 2018 ዓ/ም (ከመልሚ)

የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በተገኙበት የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የመሠረተ-ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) አራት ኪሎ፣ ባሻ ወልዴ ችሎት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘውን የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የህንጻ ግንባታ የአፈጻጸም ደረጃ በአካል ተገኝተው ጎበኙ፡፡

በይርጋለም ኮንስትራክሽን ኃ. የተ. የግል ማህበር በመገንባት ላይ ያለው የህንጻ ግንባታ አንደኛው ብሎክ ተጠናቆ ባለፈው ጥቅምት ወር ርክክብ ተደርጎ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን የቀሪ ሁለት ብሎኮች ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ የስራ ጉብኝት ነው በዛሬው ዕለት የተደረገው፡፡

ግንባታው በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ስር ባለው የፌዴራል መንግስት ህንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት አስተባባሪነት የሚመራ ሲሆን በመስክ ምልከታው በቀሩትና መስተካከል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ከአማካሪ መሀንዲሱ ጋር በጋራ በመሆን ኮንትራክተሩን ማገዝ ባለባቸው ጉዳዮች ላይ እገዛ እንዲያደርጉና ክትትላቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ በማድረግ ቀሪው ስራ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸውና ኮንትራክተሩም የሚሰጠውን አቅጣጫ በመከተል ስራውን በተሻለ ፍጥነትና ጥራት አጠናቆ እንዲያስረክብ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

አጠቃላይ የግንባታውን ቀሪ ስራ በ6 መቶ ቀናት ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ ውል ገብቶ እየሰራ ያለው ይርጋለም ኮንስትራክሽን ኃ. የተ. የግል ማህበር በቀሪው ጊዜ በተገባው ውል መሠረት አጠቃላይ ስራውን አጠናቆ ለማስረከብ በትጋት እየሰራ መሆኑን በጉብኝቱ ወቅት ገልጿል፡

Posted in: ዜና