
April 11, 2025
አዳማ፣ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ/ም (ከመልሚ) በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በከተማ አመራር፣ ፋይናንስ አገልግሎት መሪ ስራ አስፈጻሚ አዘጋጅነት ለከተማ ምክር ቤት አባላት እና ለመዘጋጃ ቤት የሥራ ሃላፊዎች የአቅም ግንባታና ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ።
በመድረኩ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዘርፉ አመራሮች እና ባለሙያዎች ከሁሉም ክልል ከተሞች የተወጣጡ የምክር ቤት አባላት፣ የመዘጋጃ ቤት የሥራ ሃላፊዎች እና ከመስተዳድሮች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የከተማ አመራር፣ ፋይናንስ አገልግሎት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ደሳለኝ ገመቹ እንዳሉት የከተሞች እና የህዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። ለኢኮኖሚ እድገት የበኩሉን እያበረከተ ነው ነገር ግን ከአገልግሎት አሰጣጥና ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ ሰፊ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ገልጸዋል ።
ይህንንም ችግር ለመፍታት የከተሞች ገቢ መጨመር እና አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን ዋናውና ወሳኙ ጉዳይ ሲሆን የምክር ቤት አባላትና አመራሮች ትልቅ ሃላፊነት ስላለባቸው በትኩረት መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል አቶ ደሳለኝ።
በመድረኩ የከተማ ምክር ቤት አባላት ብቃት እና ሚና፣ የመዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ማሻሻል እና የማዘመን አስፈላጊነት እና የከተማ ምክር ቤት አባላት ሚና እንዲሁም እነዚህን እና ሌሎች ሰነዶች ቀርበው ውይይት በማድረግ የማጠቃለያ ሀሳብ ተሰጥቶባቸዋል።
ሪፖርተር ኮከቤ ቢፍቱ
የካሜራ ባለሙያ አስመላሽ ተፈራ