
September 24, 2025
አዳማ፣መስከረም 13 ቀን 2018 ዓ/ም(ከመልሚ)
በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የመሬትና ካዳስተር መሪ ስራ አስፈጻሚ በመሬትና ካዳስተር ስራዎች የአሰራር ስርዓት እና አተገባበር ላይ በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች በዘርፉ ለሚገኙ አመራሮች እና ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና በአዳማ ከተማ ተጀምሯል ።
በስልጠናው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ ከእየክልሉ እና ከከተሞች የተወጣጡ የዘርፉ አመራሮች እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
ስልጠናውን በንግግር ያስጀመሩት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ፈንታ ደጀን እንዳሉት የከተማ ሀብት የሆነው መሬት ውድ እና አላቂ በመሆኑ ቆጥሮና መዝግቦ መያዝ መሬት በጥቂት ግለሰቦች እጅ ገብቶ ፍትሐዊነት በሌለለው መልኩ ከማስተዳደር ይታደጋል ብለዋል።
መሬት የፋይናንስ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚነሱበት እና በዘርፉ የካሳ ክፍያን አስመልክቶ በእቅድ ከሚያዘው በላይ ክፍያ የሚጠየቅበት ሁኔታዎች ይስተዋላሉ። የመሬት እና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባ አዋጅ 1381/2017 ማሻሻያ እነዝህን እና መሠል ችግሮች የሚፈታ እንደሚሆን ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘው ተናግረዋል።
በመድረኩ የመሬትና መሬት ነክ ንብረት መዝገባ አዋጅ 1381/2017 ማሻሻያ በተደረገባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች የአሰራር ስርዓትና አተገባበር፣ የመሬት እና መሬት ነክ መረጃ አደረጃጀትና ተግዳሮቶች፣ የልማት ተነሺዎች እያጋጠማቸው ያሉ ችግሮችና የካሳ ተነሺ ማቋቋምን የተመለከቱ ህጎች እና የኢትዮጵያ ከተሞች የአድራሻ ስርዓት ዝርጋታ እስታዳርድ የሚሉ ሰነዶቹ ቀርበው ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በውይይቱም በልማት ተነሺዎችን እና ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ፣ ከመረጃ አያያዝ ስርዓት ጋርም በደንብ ሊሰራበት ይገባል የሚል እና መሰል ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ከተሳታፊዎች ተነስተው ተገቢውን ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።