June 25, 2025

አዳማ፣ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ/ም (ከመልሚ)

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የድህረ ምረቃ ፕሮግራሙን በፋይናንስ በመደገፍ በባለቤትነት እየመራው ያለውን ፕሮግራም ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የዘርፉ አመራሮች እና የዩኒቨርስቲ ምሁራን በተገኙበት የምክክር ተካሄዷል።

የከፍተኛ ትምህርት ፕሮግራም በከተማና መሰረተ ልማት ዘርፍ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመፍታት ለከተሞች የበለጠ አስተዋጽኦ የሚያደርግ መሆኑን ተገልጿል።

በፕሮግራሙ ተገኝተው  ንግግር ያደረጉት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ፈንታ ደጀን እንዳሉት  ከተሞች የምግብ ዋስትናቸውን በመረጋገጥ፣ አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን፣ ጽዱ እና ውብ በመሆን ለነዋሪዎቻቸው ምቹ እንዲሆኑ በማድረግ፣ ሀብታቸውን በአግባቡ በመያዝ፣ በፕላን በመመራት፣ የቤት ልማትን በማስፋፋት፣ የተቀናጀ መሰረተ ልማት በመገንባት፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማዘመን እና  የገቢ አቅማቸውን ለማሳደግ የሚያስችል የሰው ሃይል መገንባት ይኖርብናል ብለዋል።

ይሄንኑ ታሳቢ በማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነ ገልፀው   በቀጣይም ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ ከክልሎችም ጋር በጋራ ተናበን እንሰራለን ስሉ ተናግረዋል ክቡር አቶ ፈንታ።

በመድረኩ ለከተማና መሰረተ ልማት ዘርፍ የድህረ ምረቃ ትምህርት ያበረከተው አስተዋጽኦ በተመለከተ የተጠና ጥናት እና በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የከተማ ልማት እና ምህንድስና ኮሌጅ ከከተማና መሰረተ ልማት ጋር በጋራ የተሰሩ ስራዎች ላይ የተዘጋጁ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተካሄዷል።

በፕሮግራሙ ማጠቃለያ በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የከተማ አመራር፣ ፋይናንስ እና አገልግሎት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደሳለኝ ገመቹ ከተማን የሚመራውን አካል መምራት የሚያስችል አቅም እንዲኖረው በማሰብ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ጋር የጋራ ስምምነት በማድረግ በከፍተኛ የትምህርት ደረጃ በተለያየ መልኩ ስልጠናዎች እየተሰጡ እንደሆነ እና ይሄው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል ።

ሪፖርተር: ኮከቤ ቢፍቱ
ፎቶግራፍ : አስመላሽ ተፈራ

Posted in: News