October 15, 2025

ቱሉ አራራ፣ መስከረም 27/2018 ዓ.ም (ከመልሚ)

በከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴርና በዘርፉ ተቋማት በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሰበታ ሀዋስ ወረዳ በቱሉ አራራ ከተማ የቱሉ አራራ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነቡ አራት ክፍሎች ያሉት አንድ ብሎክ የመማሪያ ህንጻና ላይበራሪ ግንባታ ተጠናቆ በዛሬው ዕለት ርክክብ የተደረገ ሲሆን በርክክብ ሥነ ስርዓቱ ላይም ለሦስት ሺህ ተማሪዎች የትምህርት መገልገያ ቁሳቁሶች (ቦርሳ፣ ደብተርና እስክርቢቶ) በስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡

በርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒን ጨምሮ ክቡራን ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የከተማና የወረዳ አመራሮች እና የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ዓባላት ተገኝተዋል ፡፡

ክብርት ሚኒስትሯ በምረቃና በስጦታ ሥነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት የተደረገው ድጋፍም ሆነ የተገነባው ህንጻ አንድ የለውጥ እርምጃ እንደሆነና የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ለተማሪዎች ውጤታማነት የበለጠ መትጋት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

የከተማዋ እና የወረዳዋ አስተዳዳሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች፤ እንዲሁም ተማሪዎችና የትምህርት ማህበረሰቡ ዓባላት ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው በእነሱ በኩል የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

የህንጻዎች ርክክብ ከተደረገ በኋላ ጉብኝት የተደረገ ሲሆን በጉብኝቱ ሂደት የት/ቤቱ ርዕሰ-መምህር ስለትምህርት ስርዓቱ አተገባበር ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ለተደረገላቸው ድጋፍ በማመስገን ት/ቤቱ በዘንድሮው ዓመት ካስፈተናቸው ተማሪዎች መካከል 5 ተማሪዎች የማለፊያ ውጤት ማምጣታቸውን ገልጸው በቀጣይ የተማሪ ቅበላ አቅማችን ስላደገና ያልነበረንን የላይበራሪ አገልግሎት በማግኘታችን የተሸለ ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን ለማፍራት የምንችልበት አቅም ስለተፈጠረልን ለተሸለ ውጤት እንተጋለን፤ ተማሪዎችም ፍላጎታቸው ስለተሟላ የበለጠ መነሳሳት አሳይተዋል ብለዋል፡፡

Posted in: News