
July 1, 2025
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19 ቀን፣ 2017 ዓ.ም (ከ.መ.ልሚ.) ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን፣ ሲምፖዚየም እና የንግድ ትርዒት በርካታ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በሚሊኒየም አዳራሽ በይፋ ተከፍቷል፡፡
ይህን ዓለም አቀፉ የኮንስትራክሽን ዓዉደ-ርዒ በይፋ የከፈቱት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ዓዉደ ርዒዉ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት እንደሚቆይ ገልጸዉ፣ በዚህ ዓለም -ዓቀፋዊ ኤግዚቢሽን፣ ሲምፖዚየም እና የንግድ ትርዒት በርካታ ሀገራት የተሳተፉበት በመሆኑ ለሀገራችን ኮንሰትራክሽን ኢንዱሰትሪ የላቀ ልምድና ተሞክሮ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚቀሰምበት መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
ክብርት ሚኒስትሯ ሁነቱን አስመልክተው እንደተናገሩት “ቢግ-5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ” የሀገር ውስጥ እና አለም አቀፍ የኮንሰትራክሽን ኢንዱስትሪ ተዋናዮች፣ የፈጠራ ባለቤቶች እና የግንባታ ግብአት አቅራቢዎች የሚሳተፉበት ሁሉን አቀፍ መድረክ በመሆኑ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን መጻኢ ዕደገት የሚኖረው ፋይዳ እጅግ የጎላ ነው ብለዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዉ በመንገድ ስራ፣ በግድብ ፣ በአየር ማረፊያ ግንባታ፣ በመስኖ፣ በቴሌ፣ በባቡር፣ በቤቶች ግንባታ፣ እና ከ60 በላይ ከተሞችን በሚያከናውኑት በኮሪደር ልማት ስራዎች ዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የሚበረክተው የስራ ዕድል ከፍተኛ መሆኑን ክብርት ሚኒስትሯ ገልጸዋል ፡፡
በዓዉደ-ርዒዉ ከብርት ሚኒስተሯን ጨምሮ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒሰትር ክቡር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፣ የኢኖቬሽ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ክቡር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራአስፈጻሚ ዮናስ አያሌው (ኢ/ር) ፣የዘርፉ ባለድርሻ አካላት እና በርካታ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ የሚካሄደውንና ለተከታታይ ሦሰት ቀናት የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን ሲምፖዚየምና የንግድ ትርዒት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ ሁነት አዘጋጅ ከሆኑት ዲ ኤም ጂ እና ኢቴኤል እንዲሁም ስትራቴጂካዊ አጋር ከሆነው ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በጋራ አዘጋጅተዋል ።
ሪፖርትር ፡-ሞገስ ዓሊ
ፎቶባለሙያ፡-ፈየ ደሜ