
May 8, 2025
ድሬደዋ፣ ሚያዚያ 25 ቀን፣ 2017 ዓ.ም (ከመልሚ) እንደ ሀገር የተቀረጸዉ የቤት ልማት ስትራቲጂ የዜጎች ፍትሃዊ የመኖሪያ ቤት ተጠቂሚነት እውን እንዲሆን የድጅታል ቴከኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸዉ ከአዲስ አበባ እና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደር፣ ከሀረሬ እና ከሶማሌ ክልል ከተማ ልማት እና ቤቶች ቢሮ ለተዉጣጡ አመራሮች የአስር ዓመት መሪ ዕቅድ እና የድጅታል ቴክኒሎጂ አተገባበርን አስመልክቶ በተሰጠ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ነዉ፡፡
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የከተማና መሠረተ-ልማት ሚ/ዲኤታ ክብርት ወ/ሮ ሄለን ደበበ እንደተናገሩት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመኖሪያ ቤትን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ በ10 ዓመቱ ውስጥ ሊያሳካቸወ ከያዛቸው ግቦች መንግስት ከሚያቀርባቸወ ቤቶች በተጨማሪ የግሉን ዘርፍ በሰፊው በማሳተፍ የመኖሪያ ቤትን እጥረት መቅረፍ እንዲቻል ሚኒስቴር መ/ቤቱ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
ይህንኑ እዉን ለማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚያወርዳቸውን አዋጆችን፣ ደንቦችን፣ መመሪያዎችንና አጠቃላይ የህግ ማዕቀፎችን ሁሉም የክልል ከተሞች በቂ ግንዛቤ ኖሮአቸው የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ተደራሽ ለማድረግ በፍጥነት መተግበር እንደሚገባ ጠቅሰዋል ሚ/ዲኤታዋ ።
በተለይ በመንግስትና በግል አጋርነት፣ በግለሰቦች፣ በማህበራት፣ በሪል ስቴት እና በሌሎች አማራጮች የመኖሪያ ቤት ችግርን መፍታ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ ኢንጅነር ኡመር ዱዋሌ በበኩላቸው ከተሞች በፈጣን እድገት ላይ ከመገኘታቸው ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ ከገጠር ወደከተማ በከፍተኛ ፍጥነት እየፈለሰ እንደሚገኝ ጠቅሰው መንግስት የህብረተሰቡን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ዘርፈ ብዝ ፍላጎቶችን ማሟላት በከተማ አስተዳደር ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በመደርኩ የአስር ዓመት መሪ ዕቅድ እና የቤት ልማት ስትራቴጂ ትግበራን አስመልከቶ የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴር የሚኒስቴር አማካሪ አቶ በየነ መለሰ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ቢሮ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብዲሳ አራርሶ በተቋማዊ ለውጥ እና ድጅታል ቴክኖሎጅ በቤት ልማት አስተዳደርና አተገባበር ዙሪያ መነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ተሳታፊዎች በርካታ ልምድ መቅሰማቸውንና ወደየራሳቸው ክልል እና ከተማ በመውሰድ የህብረተሰቡን መሠረታዊ የቤት ፍላጎት ለማሟላተ እንደሚሰሩ በመድረኩ ገልጸዋል፡፡
ከውይይቱ በኋላ በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር በኮሪደር ልማት የተከናወኑ ሰው-ተኮር የልማት ስራዎች ጉብኝት ተከናዉኗል፡፡
ሪፖርተር፡- ሞገስ ዓሊ
ፎቶ፡- አስመላሽ ተፈራ