
June 4, 2025
አዳማ፣ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ/ም (ከመልሚ) በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1320/2016 እንዲሁም በሪል እስቴት እና በቋሚ ንብረት ግመታ አዋጅ ቁጥር 1357/2017 ላይ ለአማራ ክልል በክልሉ እና በከተማ የሚሰሩ የዘርፉ አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ።
መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚ/ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሄለን ደበበ እንደተናገሩት ቤት በሀገራችን መሰረታዊ ፍላጎት በመሆኑ የቤት ልማት ፍላጎት እና አና አቅርቦት ማመጣጠን እና የህብረተሰቡን የቤት አቅርቦት ጥያቄ መመለስ እንዲቻል በዘርፉ የሚወጡ ህጎች ላይ የጠራ ግንዛቤ እንዲኖር በማሰብ መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል ።
ከዚህ ጋር በማያያዝም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1320/2016 በአማራ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች ሳይተገበር የቆየ ሲሆን ከአዲስ አበባ ተሞክሮዎች በመውሰድ በክልሉ ተግባራዊ መደረግ ይኖርበታል ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።
በፕሮግራሙ የሪል እስቴት አዋጅ፣ ደንብና የቤት ስትራቴጂ፣ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1320/2016 የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነድ እና የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ ትግበራ ዙሪያ ከአዲስ አበባ ከተማ ተሞክሮ ቀርቧል።
በቀረቡት ሰነዶች ከተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ቀርበው ሰፋ ያለ ውይይት በማድረግ በክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ የማጠቃለያ ሀሳብ የእለቱ መርሀ ግብር ተጠናቋል።
ሪፖርተር ኮከቤ ቢፍቱ
የካሜራ ባለሙያ ፈዬ ደሜ